መነሻ ገጽዜናትንታኔ‹‹ውሃ ማጣትም ሌላኛው ጦርነት ሆኗል››

‹‹ውሃ ማጣትም ሌላኛው ጦርነት ሆኗል››

የከተማው ነዋሪዎች በጠዋት ተነስተው በርካታ ባዶ ጀሪካን ሰብስበው ይተማሉ። አንዳንዶቹ ባጃጁን በጀሪካን ሞልተው በፍጥነት ይነዳሉ። ሌሎቹ ደግሞ ጋሪ ጭነው ከባጃጁ ለመድረስ ይጣደፋሉ። መሰሎቻቸው ጋሪ ለመጫን ባይበቁም አንድ አህያ ላይ ከኹለት እስከ ስድስት ጀሪካን ጭነዋል። ከዚህ የቀሩት በእግር ለመጓዝ የተገደዱ መስለው ቁና ቁና እየተነፈሱ ከኋላ ይከተላሉ።

እድሜያቸው ከስምንት እስከ 12 ዓመት የሆኑ ሕፃናት የጉዞው ተሳታፊ ናቸው። የሚጓዙት ከተሽከርካሪዎች ጎን በጎን ነው። አሽከርካሪዎችም በዝምታ የሚሄዱ አይደሉም፣ የሚያሰሙት ጥሩምባ (ክላክስ) የትራፊክ ፍሰቱ የተስተጓጎለ መሆኑን ያሳብቃል። የተጫኑት አህዮች ወደ ዋናው መስመር ሲገቡ ስፍራው በተሽከሪካሪ ክላክስ ጩኸት ይናጣል።

ሰዎቹም እንስሳቱ ከመኪና መንገድ እንዲወጡ ለማድረግ ወደ አስፓልቱ ለመግባት ይገደዳሉ። አደጋ ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው የሚያሳውቁት ሁሉም ተጓዦች ከፍርሃታቸው አንጻር ራሳቸውን ይዘው አንገታቸውን ሲደፉ ይስተዋላሉ። አንዳንዶቹ “መቼም እግዚአብሔር እየጠበቀን እንጂ፣ በዚህ ወቅት አደጋ አይፈጠርም ማለት እኮ ሞት የለም ብሎ መገዳደር ነው” ይላሉ። እንዲህ ሆነው መዳረሻቸውን ሆርማት ከተባለ ወንዝ አደረጉ።

አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑ ጉዞው ይበልጥ በውሃ ጥም እንዲቃጠሉ አሳልፎ የሰጣቸው ነዋሪዎቹ፣ ወረፋ ለመጠበቅ ሰከን ማለት ተስኗቸው ለመጠጣት ይሽቀዳደማሉ።

ወንዙ ከቆቦ ከተማ ውጪ የሚገኝ ሲሆን፤ ከደጋማው ክፍል ከሚገኝ ቋጥኝ የሚፈስ ውሃን የሚመጸውት ነው። ከወራጁ ውሃ ጎን በጎን ጫር ጫር አድርገው ውሃ በማፍለቅ (ምንጭ በማመንጨት) ተጓዦቹ ውሃ ቀድተው ይመለሳሉ። ውሃ ከተሸከሙት ሰዎች መካከል ኤፍሬም ሙላው የተባለው የ10 ዓመት አዳጊ “እናቴ ወልዳለች ከሌሎች ሰዎች በተለየ መልኩ ውሃ ያስፈልጋታል። አሁን እኔ ውሃ ይዠ እስከምደርስላት እየጠበቀችኝ ነው። ውሃ ማጣት ሌላኛው ጦርነት ሆኗል” ሲል በልጅነት አንደበቱ ተናገሯል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከሆነ፤ ቦታው በጦርነት ውስጥ ሳለ የዝናብ ውሃም አቁረው የጠጡበት ጊዜ ነበር።

ታዲያ ይህ ድርጊት ስፍራው በጦርነት ቀጠና በነበረበት አምስት ወራት እንዲሁም ነጻ ከወጣ በኋላም ለተከታታይ አምስት ወራት በላይ ያስቆጠረ ክስተት መሆኑን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ አንደበት በአካል አረጋግጣለች።

የጦርነቱ ውጤት – ከህልፈተ ሕይወት እስከ ውሃ እጥረት
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24/2013 ድንገተኛ ጥቃት አደረሰ። ጥቃቱን ተከትሎ የትግራይ ክልል ለስምንት ወራት መንግሥት “የሰላም ማስከበር ዘመቻ” ብሎ በጠራው ጦርነት ውስጥ ቆየች።
“በደረቅ አበሳ ዕርጥብ ይቃጠላል” እንዲሉ፣ ሕወሓት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ትንኮሳ የትግራይ ክልል ሕዝብን ለስምንት ወር ለርሃብና ስቃይ መዳረጉ በወቅቱ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ነበር።

ታዲያ መንግሥት በበኩሉ ሽብርተኛ ብሎ የፈረጀው የሕወሓት ቡድን የሰላም ማስከበር ዘመቻውን ኃላፊነት የወሰደው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ “አፈር ዱቄት አድርጎታል። ድጋሚ ለጥቃት እንዳይነሳ አድርጎ ቀብሮታል” ብሎ መከላከያ ሠራዊቱ ሰኔ 21/2013 መቀሌን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል።

መንግሥት ሰላም አስከባሪ የተባሉት አካላት የትግራይ ክልልን ለቀው እንዲወጡ መመሪያ የሰጠው “ለገበሬው የእርሻ ጊዜ ፋታ ለመስጠት” ነው ብሎ ነበር።

“ሥልታዊ ማፈግፈግ” በሚል ሰበብ፣ የመከላከያ ሠራዊት ለጠላት ከባድ መሣሪያ እያስረከበ በመሸሹ አርሶ አደሩ እንዲዋጋ ሲገደድ ግን “ለገበሬው የእርሻ ፋታ ለመስጠት” የሚለው ቃል ሌላ ሴራ እንደነበረው የፖለቲካ ተንታኞች ብቻ ሳይሆኑ አርሶ አደሮቹም በተደጋጋሚ ይናገራሉ።
የሰላም ማስከበር ዘመቻው ወደ ለየለት ጦርነት አደገ። የሕወሓት ታጣቂዎች ቀስ በቀስ ከመቀሌ ተነስተው ወደ አፋርና አማራ ክልል ተስፋፉ።

በሐምሌ ወር 2013 በአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ሥፍራዎች የተጀመረው ጦርነት እየተስፋፋ መጥቶ የአማራ ክልል የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ለወራት በሕወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ሆኑ።

“ኹለት ዝሆኖች ሲፋለሙ ምስኪኑ ሳር ይጎዳል” እንዲሉ፣ ሥልጣን ላይ ለመውጣት በሚደረገው ስግብግብነት ጉልበተኞች በሚሰነዝሩት ጥቃት በርካታ ንጹሓን ዜጎች ዳግም ላይመለሱ እንዳሸለቡ በየወቅቱ የሚሰሙት ዜናዎች ሕያው ምስክር ናቸው። ጡት ከአፋቸው ያልጣሉ ሕጻናት ተስፋ ባለመቁረጥ የእናቶቻቸውን መምጫ ነጋ መሸ በመጠባበቅ ዐይናቸው ውሃ እንዲያቀር ተገደው ይታያሉ።

“ትልቅ እያለ እንዴት ወጣት ይሙት”? ሲሉ ራሳቸውን የሚጠይቁ አዛውንት ጧሪዎቻቸውን በጦርነቱ መነጠቃቸውን ይናገራሉ። የአቅመ ደካሞችና የልጃገረዶች መደፈር ሌላኛው ጦርነቱ ያስከተለው ጠባሳ ነው።
በሌላ ጎን የሞት ዕጣ ፈንታ ያልደረሳቸው ዜጎች በበኩላቸው መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ከአምስት ወር በላይ ሰላም ወዳለባቸው ሥፍራዎች ለመፈናቀል ተገደዋል።

በቆላማው አካባቢ ከራያ አላማጣ ወደ ራያ ቆቦ፤ ከራያ ቆቦ ወልድያ፤ ከወልድያ ደሴ፤ ከደሴ ኮምቦልቻ፤ ከኮምቦልቻ ደብረ ብርሃን እንዲሁም በከፊል ከደብረ ብርሃን አዲስ አበባ ድረስ ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን፤ ደብረ ብርሃን ሲደርሱ መንግሥት ባሉበት እንዲጸኑ ባስተላለፈው መልዕክት መሠረት ወደ አዲስ አበባ እንዳያልፉ መደረጋቸው ይታወሳል። ከደጋው በኩል ያሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ከላሊበላ ወደ ኩል መስክ፤ ከኩል መስክ ወደ ሙጃ፤ ከሙጃ ወንዳይ ከዚህም አልፈው ወደ ባህር ዳር ለመፈናቀል ተገደው ነበር።

ምንም እንኳ መንግሥት፤ የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የበኩላቸውን የምግብ፤ የመጠለያና፤ የአልባሳት ድጋፍ ከመቸር ባይቦዝኑም፣ የሚያሻቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ሊያገኙ አለመቻላቸውን ተፈናቃዮች በተደጋጋሚ ሲለፍፉ ተስተውለዋል።

በጥምር ኃይል ጦርነቱን ለመመከት ባደረጉት ርብርብ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ተፈናቃዮቹ ወደየቀያቸው ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ሺሕ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል። ቤታቸውን ለወራት ለቀው መቆየታቸውን ተከትሎ ንብረት ተዘርፏል። መሠረተ ልማት ወድሟል። ኢሰመኮ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ሆነ ተብለው የተፈፀሙ ግድያዎችን ሳይጨምር በጦርነቱ ሳቢያ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ንፁሀን ሰዎች ለቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት መዳረጋቸውን በምርመራ ማረጋገጡን መጋቢት 2/ 2014 አሳውቋል።
እንደ ሪፖርቱ ምልከታ ከሆነ፤ ምርመራው የተካሄደው በክልሎቹ ባሉ ስምንት ዞኖች ከ50 በላይ የሆኑ ቦታዎችን በማሰስ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

በዚህም በአማራ ክልል 40 ሆስፒታሎች፣ 453 የጤና ተቋማት፣ አንድ ሺሕ 850 የጤና ኬላዎች፤ በድምሩ 2 ሺሕ 343 የጤና ተቋማት፤ በአፋር ክልል ደግሞ በድምሩ 66 የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል ተብሏል።

ነዳጅና ውሃ
በሕወሓት ቁጥጥር ስር የነበሩና በኋላ ነጻ የወጡ ሰሜን ወሎ አካባቢዎች በጦርነቱ የደረሰው የመሠረተ ልማት ውድመት ጥገና ተደራሽ ያልተደረገባቸው ስፍራዎች አሉ።
ለአብነትም ራያ ቆቦ እና ተኩለሽ ከተማ ለአምስት ወር በሕወሓት ቁጥጥር ስር ቆይተው አሁን ነጻ ወጥተዋል። ሆኖም ግን የወደሙ የውሃ እና የመብራት መሠረተ ልማቶች ባለመጠገናቸው ዜጎች ችግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ነዋሪዎቹ ከጦርነቱ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች እያፈገፈጉ ቆይተው አንጻራዊ ሰላም ሲሰፍን ወደየቀያቸው ከተመለሱ ከታህሳስ 11/2014 ጀምሮ ውሃ የሚያገኙት በጀነሬተር እየሳቡ የነበረ ቢሆንም፣ መፍትሄ ባልተቸረው የነዳጅ እጥረት ምክንያት የውሃ አገልግሎት እያገኙ አይደለም።

ታዲያ ጦርነቱ ባለመቋጨቱ የወደሙ የውሃ ልማትና መብራት ጥገና አለመደረጉ ነዋሪዎቹን ለችግር ዳርጓል። ከነዚህም መካከል መልሶ ጦርነት የመቀስቀስ ስጋት ያለበት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኝው ቆቦ ወረዳ አንዱ ነው። በጦርነቱ መንስኤ በአካባቢው የሚገኙ መሰረተ ልማት መውደም የተነሳ ነዋሪዎች በከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግር እየተሰቃዩ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ አረጋግጣለች። ለነዋሪዎች የውሃ መጠጥ ለማቅረብ የከተማዋ መስተዳድር ጥረት ቢያደርግም የውሃ ፓምፕ ለማንቀሳቀስ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ሙከራውን እያደናቀፈ ይገኛል።

ለማኅበረሰቡ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ በቀን 16 ሰዓት በጀነሬተር መሳብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ለዚህም በሰዓት 22፤ በቀን 352፤ በወር 10 ሺሕ 560 ሊትር ነዳጅ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን የነዳጅ እጥረቱን ተከትሎ አገልግሎቱ እየተቆራረጠ መሆኑን ሁኔታውን በጥልቀት ሲከታተሉ የነበሩ የቀድሞ የቆቦ ከተማ ከንቲባ አዲሱ ወዳጆ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ 34 ብር ሲሆን፤ ይህም ሲሰላ ለማኅበረሰቡ ውሃ ለማዳረስ በወር 359 ሺሕ 40 ብር ገደማ ይጠይቃል።

ከነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ የሚሰማው ቅሬታ፤ የወደመው መብራት አለመጠገኑን ተከትሎ “በጨለማ ውስጥ ነው ያለነው። የውሃ ችግርም እስከ አሁን መፍትሄ አልተሰጠውም። አንድ ጀሪካን ውሃ 20 ብር ነው የምንገዛው” የሚል ነው።
ውሃ የሚመጣው በፈረቃ ሲሆን፤ የማያገኙ ስፍራዎችም አሉ። ውሃ የማያገኙት ሰዎች ከከተማው ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ከሚገኙ ነዋሪዎች እየገዙ መሆኑን አብራርተዋል።
ኃይሉ ደጀን የተባሉ የቆቦ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ አንድ ጀሪካን ውሃ 20 ብር እንደሚገዙና ለስምንት የቤተሰብ አባላቸው በቀን ቢያንስ አራት ጀሪካን እንደሚያስፈልግ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የሚወጣው ወጭ በቀናት ሲሰላ ቀላል አይደለም የሚሉት ኃይሉ፤ በቀን 80፤ በሳምንት 560 እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የውሃ አቅርቦት ችግር ያለባቸው ነዋሪዎቹ ውሃ የሚያገኙት ብዙውን ጊዜ ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሆርማት ወንዝ ሲሆን፤ ውሃውም የንጽህና እንከን እንዳለበት አልደበቁም። በመሆኑም የሚቀዱትን ውሃ ለመጠጥ የሚጠቀሙት እያፈሉ እንዲሁም በጀኔሬተር ተስቦ የሚያገኙትን ለመጠጥ ከወንዝ የሚቀዱትን ለሌላ ጥቅም በማዋል ነው።

- ይከተሉን -Social Media

የተኩለሽ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ መብራትና የውሃ አገልግሎት ማግኘት ካቆሙ 10 ወር እንዳስቆጠሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
እስከ አሁንም የወፍጮ፤ የኔትወርክ፤ የውሃ እንዲሁም መብራት አገልግሎት የለም።

የሰዎች የሕይወት ጥራት በውሃ እጥረት ምክንያት እንደተጎዳና የተበከለ ውሃ በመጠጣት ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች 82 በመቶው የተሻሻለ ውሃ ተደራሽነት ከሌላቸው ቦታዎች መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አመላክቷል።
የዓለም የውሃ ቀን ከ1993 ጀምሮ በየአመቱ መጋቢት 22 ቀን የሚከበር ሲሆን፤ በወቅቱ የተሰጡ መረጃዎች በመፈናቀል እንዲሁም በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በዓለማችን ከ2.2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ንጹህ ውሃ እንደማያገኙ ያብራራል።

ታዲያ ይህ ችግር በጤና ላይም እክልን ሲፈጥር ይስተዋላል። ለአብነትም በአማራ ክልል ውስጥ የምትገኘው ወልዲያ ከተማ በጦርነቱ ቀጠና በነበረችበት ወቅት ያልተፈናቀሉት ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ከወንዝ እየቀዱ በመጠቀማቸው ለአተት በሽታ ተዳርገው እንደነበር አዲስ ማለዳ በወቅቱ ዘግባለች።
በቆቦ ከተማ ግን እስከ አሁን የተጋነነ የጤና እክል እንዳልተከሰተ ከቆቦ ጤና ጣቢያ የተገኘው መረጃ አመላክቷል። ‹‹ወተር ኤድ›› የተሰኘ ድርጅትም 60 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በአቅራቢያው ማግኘት እንደማይችል ያመላክታል።

ድርጅቱ ባወጣው መረጃ መሰረት በውሃ አቅርቦት እየተሻሻሉ ካሉ 10 አገራት መካከል ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ደረጃ ብትይዝም፣ አብዛኛው ሕዝቧ በቅርብ ቦታ ውሃ አያገኝም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንኳ በገጠሩ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዕድሉን ማግኘት ባይችሉም፤ በከተማ የሚገኙ ዜጎች በየቤታቸው የውሃ አገልግሎት ያገኛሉ።

በገጠሩ አካባቢ ውሃ የሚቀዱት ሴቶች ሲሆን፤ ውሃ የሚያገኙት ከኹለት ሰዓት በላይ ወደ ወንዝ ተጉዘው መሆኑን አዲስ ማለዳ በተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተዘዋውራ አይታለች።
በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የናጠጡ ሀብታም ናቸው የሚባሉ ሰዎች ውሃ የሚቀዱት በግመል ሲሆን፤ መካከለኛ ናቸው የሚባሉ ሰዎች ደግሞ በአህያ እንዲሁም ለዚህ አገልግሎት የሚውል እንስሳት የሌለቸው ሰዎች ደግሞ ራሳቸው ወንዝ ወርደው 25 ሊትር ጀሪካን ጀርባቸው ላይ አዝለው ነው።
ታዲያ በጀርባቸው ለመቅዳት ድካም ስለሚሰማቸው ለገጠሩ ማኅበረሰብ ውሃ የ‹ቅንጦት› ሆኗል። ለምግብ ማብሰያና ለመጠጥ እንጂ ብዙም ለንጽህና የመጠቀም ዕድሉ የላቸውም።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተስፋዬ አበበ የተባሉ አርሶ አደር፣ “በጭቃና በአቧራ እየተጨማለቅን እንኳ የምንታጠብበት ውሃ በቅርቡ ማግኘት አንችልም። በከተማ የሚኖሩ ዜጎች የሚውሉት ቢሮ በመሆኑ ምንም አይነት አቧራ አያገኛቸውም። ነገር ግን፣ ውለው ሲገቡ እንኳን እግራቸውን ሙሉ አካላቸውን የሚታጠቡበት ብቁ የውሃ አቅርቦት ከቀያቸው እንደሆነ እንሰማለን። ሲባዝን የሚውለውን አርሶ አደር ግን መንግሥታችን የማይመለከተው ለምንድን ነው? በእውነት የከተማው ሕዝብ ገበሬው ጤናማ ሆኖ ካላመረተ መኖር ይችላልን?” ሲሉ አውስተዋል።
የገጠሩ አካባቢ በአቅራቢያው ውሃ ማግኘት ሳይችል ዘመናት ቢቆጠርም፤ የከተማው ነዋሪ ግን በየቀዬው ውሃ ያገኝ ነበር።

የውሃ ዕጥረት በጤና ተቋማት
በአማራ ክልል 40 ሆስፒታሎች፤ 453 የጤና ተቋማት፤ አንድ ሺሕ 850 የጤና ኬላዎች በጠቅላላው ኹለት ሺሕ 343 የጤና ተቋማት፤ በአፋር ክልል 66 የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ እንደሆኑ ኢሰመኮ በመጋቢት 2/2014 ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ታዲያ የወደሙትን ተቋማት እንደገና በማቋቋም አገልግሎት መስጠት ቢጀመርም የቁሳቁስና የመሠረተ ልማት ውድመት አገልግሎቱን እያስተጓጎለ እንደሚገኝ ተስፋ ባለመቁረጥ ችግሩን እየተጋፈጡ ያሉ አካላት ይናገራሉ።

የጤና ተቋማት 24 ሰዓት የውሃ አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባቸው ለሥራው በቅርበት ያሉ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። የውሃ መሠረተ ልማት በጦርነቱ ወድሞ ጥገና ያልተደረገበት ቦታዎች ነዋሪዎቹ ለመጠጥ የሚሆን ውሃ የሚያገኙት ከወንዝ በመቅዳት እንዲሁም በጀነሬተር ከሚሳበው ውሃ በፈረቃ ሲደርሳቸው ነው። ቢሆንም ግን፣ ይበልጥ የውሃ አቅርቦቱ የሚያፈልጋቸው የጤና ተቋማት በችግር ውስጥ እንደሆኑና ዕርዳታ እንደሚያሻቸው ገልጸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ባመላከተው መሠረት፣ የጤና መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው በአማራ ክልል መቄት ወረዳ ብቻ ስምንት ነፍሰ ጡር እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
የቆቦ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ብርሃኑ ተንሳው በበኩላቸው ተመሳሳይ ክስተት እንዳጋጠማቸው ነው የገለጹት። እንደ ኃላፊው ገለጻ ከሆነ፤ አካባቢው ገና የጦርነት ስጋት ያለበት መሆኑን ተከትሎ ባለመረጋጋቱ ቁጥራቸውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ ግን አልደበቁም። በርካታ

እናቶችም በጤና ተቋማት ሊገለገሉ ባለመቻላቸው ሦስት አራት ቀን አምጠው በቤታቸው የወለዱበት አጋጣሚ እንደነበርም ተብራርቷል።
እናቶች ከቤት መውለዳቸውን ተከትሎ የኤች ኤይ ቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍ እድል ሰፊ እንደነበርም ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አሁን አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም በጦርነቱ የወደመው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ባለመደረጉ፣ የውሃ አቅርቦትና የላብራቶሪ አገልግሎት እየተቆራረጠ ነው የሚሉት ብርሃኑ፤ በቆቦ ጤና ጣቢያ ብቻ 18 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በጦርነቱ መውደሙን ጠቅሰዋል።
ኃላፊው በተናገሩት መሠረት በተለይም የላብራቶሪና የውሃ ችግር በመጋረጡ ከጦርነት የተረፈውን ሕዝብ ለማገልገል አስቸጋሪ ሆኗል።

ነዋሪዎቹ በበኩላቸው የውሃ እጥረቱ የጤና ተቋማት ላይ ክፍተቱ እንደበረታ ገልጸዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል ሙሉ አራጌ የተባሉት እናት በጤና ጣቢያው መጸዳጃ ቤት ውሃ ባለመኖሩ ሕሙማን ሲቸገሩ ማየታቸውን መስክረዋል።

ኧረ ነዳጅ!
ወደ ጤና ጣቢያ የሚያቀኑትን ሕሙማን ለማስተናገድ የውሃ አቅርቦት ማግኘት የሚቻለው በነዳጅ አማካኝነት በሚመነጭ መብራት መሆኑን የገለጹት የቆቦ ጤና ጣቢያ ኃላፊ፤ ነዳጅ የሚያመጡት ከወልዲያ ከተማ እንደሆነና በቀን 50 ሊትር እንደሚያሻቸውም ተናግረዋል።
የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ 34 ብር ነው የሚሉት ብርሃኑ፤ በቀን ለሚጠቀሙት 50 ሊትር ነዳጅ አንድ ሺሕ 700 ብር፤ በሳምንት ለሚጠቀሙት 350 ሊትር ነዳጅ 11 ሺሕ 900 ብር እንዲሁም በወር ለሚጠቀሙት አንድ ሺሕ 500 ሊትር ነዳጅ ለመግዛት 51 ሺሕ ብር ይጠይቃል ነው ያሉት።

የወደሙ ቁሳቁችንና መድኃኒቶችን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ለማሟላት 100 ሺሕ ብር ብቻ ነው የተበጀተው የሚሉት ኃላፊው፣ ይህ በቂ እንዳልሆነና የበጀት ዕጥረት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ብርሃኑ አክለውም፣ በጤና ጣቢያው ውስጥ በእያንዳንዱ ክፍል ውሃ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ አሁን ግን አንድ ታንከር አንድ ቦታ ላይ አስቀምጠን ነው የምንቀዳው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች