ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት አድርጋው ከነበረ ተስፋ አንጻር አሁናዊ ሁኔታዋ በሕልም እንኳ ቢመጣ ‹ሕልም እልም!› የሚባልና በብዙዎች ሐሳብ ይሆናል ተብሎ የማይገመት ነው። ይልቁንም በሰሜኑ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የታዩ ግጭቶች፣ የብዙዎች ሞትና መፈናቀል፣ እንግልትና መከራ ወትሮም ሲጠየቅ የነበረውን ‹ወዴት እየሄድን ነው?› ጥያቄ በአዲስ መልክ ያስነሳ ሆኗል።
መንግሥት በበኩሉ ተቃውሞዎችንና ቅሬታዎችን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት፣ ‹እኔ የማደርገውን አውቃለሁ!› በሚመስል አኳኋን የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ አፈናዎችና እገታዎች በመንግሥት እየተፈጸሙ ነው። ጋዜጠኞች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችና በተለያየ አደረጃጀት ውስጥ ያሉ ሰዎች ታሰሩ፣ ተያዙ፣ ታፈኑ የሚሉ ዜናዎች በብዛት እየተሰሙ ነው። ይህንን ጨምሮ በተለይ በአማራ ክልል መንግሥት ‹ሕግ የማስከበር ዘመቻ› ነው የያዝኩት ይበል እንጂ፣ ከተቃውሞ የዳነ አይደለም። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ከዚሁ የ‹ሕግ ማስከበር ዘመቻ› ከተባለና በብዙዎች ተቃውሞ ከገጠመው የመንግሥት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሰዎችን በማናገርና የቀደሙ መግለጫዎችን በማጣቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ነገር አድርጎታል።
በአማራ ክልል በመገባደድ ላይ በሚገኘው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የፌዴራል መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት በጋራ እያካሄድነው ነው ባሉት “የሕግ ማስከበር እርምጃ” ከአራት ሺሕ 500 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የክልሉ መንግሥት ከሰሞኑ መግለጹ የሚታወስ ነው። መንግሥት እያካሄድኩ ነው በሚለው ”የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ከተለያየ ወገን ትችትና ተቋውሞ ቢገጥመውም፣ የክልሉ መንግሥት “አንጸባራቂ ድል” እያገኘሁበት ነው ብሏል።
መንግሥት በክልሉ “በሕግ ማስከበር ሥም” እያካሄደ ያለውን ጅምላ እስር በሚመለከት፣ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም የማኅበረሰብ አንቂዎች እንደሚያሳስባቸው እየገለጹ ነው።
የመንግሥት ሕግ ማስከበር በአንድ ሰሞን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በገፍ የታሰሩበትና መንግሥትን በመተቸት የሚታወቁ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችንና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የቀድሞ ኃላፊ የነበሩትን ብርጋዴል ጄነራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ በርካቶች የተያዙበት ሁኔታ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያውጡ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት በጋራ እያካሄድን ነው የሚሉት “የሕግ ማስከበር እርምጃ” በመላው አማራ ክልል በሚባል ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ ከሰሞኑ ከሰጣቸው ማብራሪያዎች መረዳት ይቻላል። የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥት በክልሉ እየተካሄደ ባለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ቀደም ሲል በብሔራዊ ጸጥታ ምክር ቤትና ከሰሞኑ በአማራ ክልል ጸጥታ ምክር ቤት “የሕግ ማስከበር ሥራ” እንዲሠራ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የሕዝብ ጥያቄ የሆነውን የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ፣ ጉዳዩ በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን አስተናግዷል። ይህንንም ተከትሎ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች የተገደሉበትና የቆሰሉበት ሁኔታ መከሰቱን አዲስ ማለዳ በተለይ ከወልዲያ እና ከመራዊ ከተማ ነዋሪዎች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
እንደ ወልዲያ ባሉ ከተሞች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ባሉት እርምጃ፣ “ፋኖን እያሳደዱ ነው” በሚል የወልዲያ ከተማ ወጣቶች “ፋኖን አትንኩብን” በማለት ተቋውሞ በማሰማታቸው ቢያንስ አምስት ሰዎች ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውንና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች መቁሰላቸውን አዲስ ማለዳ ከወልዲያ የዐይን እሟኞች ሰምታለች።
የተቃውሞ ድምጾች
የክልሉ መንግሥት በመላው የክልሉ አካባቢዎች የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ እያካሄድኩ ነው ይበል እንጂ፣ በመንግሥት እርምጃ ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎች አልተቀበሉትም። እንደውም ቀደም ብሎ ሲራገብ የነበረውን “መንግሥት ፋኖን ትጥቅ ሊያስፈታ ነው” የሚለው ብዥታ ተግባራዊ እየተደረገ ነው በማለት የተቃውሞ ድምጻቸውን በተለያየ መንገድ እያሰሙ ነው።
ይህ ፋኖ የተባለው አደረጃጀት በተለይ ሕወሓት በአማራ ክልል ወረራ ከፈጸመ በኋላ በተጠናከረ ሁኔታ በየአካባቢው እየተደራጀ መሄዱ የሚታወስ ነው። የክልሉ መንግሥት ሕወሓት ወደ አማራ ክልል በገባበት ወቅት ባደረገው የክተት ጥሪ፣ ፋኖ ከመከላከያ ሠራዊትና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በጋራ በመሰለፍ መዋጋቱን የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።
የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደሚሰማው ከሆነ “ትክክለኛ ፋኖ” እና “በፋኖ ሥም የሚነግዱ ቡድኖች” ብሎ በኹለት ይከፍላቸዋል። ከዚህ ቀደም ሲገልጽ እንደነበረው፣ “በፋኖ ሥም የሚነግዱ ቡድኖች” በሚላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ሲገልጽ ነበር። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ “የክልሉ መንግሥት ፋኖዎችን ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ የሚያሳድድ እና የሚያዋክብ አይደለም” ብለዋል። ይበሉ እንጂ፣ የሚሰሙት ተቃውሞዎች ግን “ፋኖን የመበተንና፣ ትጥቅ የማስፈታት ሥራ ነው እየተሠራ ያለው” በሚል የመንግሥትን እርምጃ የሚተቹ ናቸው።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ “በአማራ ክልል በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያና ገንዘብ ዝውውር፣ በቡድን ተደራጅቶ ግለሰቦች ያፈሩትን ሀብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ላይ የተሰማሩ፤ በነፍስ ግድያ የሚጠረጠሩ፣ አንዱን ሕዝብ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክልሉ እንዳይረጋጋ በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል” ብሏል።
ይሁን እንጅ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕጋዊነትና ተገቢነት ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ብዙዎች አውግዘውታል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ) በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል ብሏል።
ኢሰማኮ በመግለጫው፣ “የተወሰኑት ተጠርጣሪ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻቸው የተጎበኙና በተለያየ የጊዜ መጠን ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን ተመልክቻለሁ” ብሏል። በተለይም፣ በአማራ ክልል በርካታ ታሳሪዎች ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸውና ከመደበኛ እስር ቦታዎች ውጭ ጭምር በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንኳን ለማወቅ መቸገራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
የዚህ አይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገልጸዋል። “በተለይም የፌዴራልም ሆነ የክልል የጸጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ ይገባል። እንዲሁም በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ እንዲደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል” ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ የተወሰኑ የአብን አባላት ግንቦት 12/2014 ባወጡት መግለጫ፤ “መንግሥት እገታና ስወራ እየፈጸመ ነው” ሲሉ ከስሰዋል። “በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አባላትና አመራሮች፣ በፋኖ አባላት፣ በሕጋዊ ታጣቂዎችና ወጣቶች እንዲሁም አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ የጦር መኮንኖችንና የጸጥታ አመራሮች ላይ የሚፈጸመው መንግሥታዊ እገታና ስወራ በአስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ ሰበብ በማንነታቸው ብቻ የታገቱ አካላትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን” ብለዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከሰሞኑ ጋዜጠኞች እና ማኅበረሰብ አንቂዎች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑ አሳስቦኛል ማለቱም የሚታወስ ነው። ኤምባሲው የጅምላ እስሮቹን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባቀረበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የፌዴራል እና የክልል ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል አለባቸው ብሏል።
እንዲሁም እናት ፓርቲ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ መንግሥት በአማራ ክልል እየወሰደ ያለውን እርምጃ ኮንነዋል። እናት ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ “አገር ተደፈረች ብለው ከጡረታቸው እየተመለሱ አገር ለማዳን የታገሉ ጀግኖቻችንን፣ ጋዜጠኞችን ማፈን፣ ማጥፋትና ማሳደድ እንደ ትልቅ ክህደት የሚታይና የአሁኑ የትዕይንት ክፍል ምን አልባትም ወደማለቂያው እየቀረበ ይሆን ወይ? የሚያስብል ነው። ሥርዓቱ ከመወደድ ይልቅ መጠላትን፣ ከሕጋዊ አካሄድ ይልቅ አፈናን፣ ከመከበር ይልቅ መፈራትን ከመረጠ በሚያስገርም ፍጥነት ከሕዝብ እየተነጠለ፣ ውድቀቱንም እያፋጠነ፣ ወዲህም የሰውን ልጅ ውድ ሕይወት እየቀጠፈ መቀጠሉ አይቀሬ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻም” ብሏል።
ባልደራስ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ “መንግሥት በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በፋኖ ላይ የከፈተው የመግደልና የማሳደድ ዘመቻ ቀይ መስመር ያለፈ አደገኛ አካሄድ መሆኑንና መጨረሻው እንደማያምር ሊታወቅ ይገባል። ፋኖና የአማራ ሕዝብ የሚነጣጠሉ አይደሉም። ፋኖ ላይ የተነጣጠረ ማንኛውም እርምጃ በአማራ ሕዝብ ላይ ብሎም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ነው። ፋኖ ለአማራ ሕዝብ ህልውና ብሎም ለአገሩ አንድነት ደሙን የገበረ ሕዝባዊ ኃይል እንጂ አሸባሪ አይደለም” ነው ያለው።
የመንግሥት የሕግ ማስከበር አካሄድ ጥያቄ ቢነሳበትም የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ የሕግ ማስከበር እርምጃውን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደማይታገስና እርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
መንግሥት ከአማራ ክልል ምን አለው?
በአማራ ክልል መንግሥት እያካሄደ ያለው ሕግ ማስከበር ነው ይበል እንጂ፣ ጉዳዩ ጥያቄ ከማስነሳት አልፎ ሌላ ችግር እንዳያስከትል ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። መንግሥት “ሕግ ማስከበር” ሥራዬን ለማደናቀፍ የሚደረግ ማንኛውንም ጥረት አልታገስም ማለቱን ተከትሎ ባሳለፍነው እሁድ (ግንቦት 14/2014) በአማራ ክልል የተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጣ ቅስቀሳዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ደርተው ነበር። ይሁን እንጂ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በዋዜማው ባወጣው መግለጫ የታሰበው የተቃውሞ ሰልፍ አልተካሄደም።
የመንግሥት እርምጃ እና የተቋውሞ ድሞጾች መሰማታቸው አሁንም እንደቀጠለ ነው። መንግሥት ሰላም ለመፍጠር እያካሄድኩ ነው የሚለው እርምጃ ሌላ ስጋት ጭሯል። አዲስ ማለዳ ውዝግብ ስላስነሳው ጉዳይ የተለያዩ ወገኖችን ሐሳብ ለመስማት ባደረገችው ጥረት “መንግሥት እያሳደደን ነው” የሚሉ የፋኖ አባላትን አነጋግራለች።
አዲስ ማለዳ “ለደኅንነቴ ስለምሰጋ ሥሜን አትጥቀስ” በማለት ሥማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ፣ ሕወሓት አማራ ክልል በገባበት ወቅት ግንባር ድረስ ዘምተው ሲያስተባብሩና ሲዋጉ የነበሩ የፋኖ አባል አነጋግራለች። መንግሥት በክልሉ እያካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን የፋኖን አደረጃጀት ለመበተን መሆኑን የፋኖ አባሉ ይናገራሉ።
“በሕግ ማስከበር የዳቦ ሥም፣ ፋኖን ትጥቅ የማስፈታት፣ የማሳደድና መሣሪያ የማሳጣት ሥራ እየተሠራ ነው” የሚሉት የፋኖ አባሉ፣ መንግሥት ትክክለኛ ፋኖን አልነካም ቢልም መሬት ላይ ያለው ነገር የተለየ ነው ይላሉ። በዚህም በተለያየ ጊዜ ሥልጠና ወስደው የፋኖ አባል የሆኑ ወጣቶች ለእስርና መሳደድ መዳረጋቸውን ይናገራሉ።
አዲስ ማለዳ በወልዲያና መራዊ አካባቢ ስላለው ሁኔታ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የፋኖ አባላትን ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ የፋኖ አባል የሆኑ ወጣቶች ወደ ጫካ እየገቡ መሆኑን ነው።
መንግሥት የሕዝብ ጥያቄ የሆነውን የሕግ ማስከበር ሥራ እየከወንኩ ነው ማለቱን ቢቀጥልም፣ በሕግ ማስከበሩ ላይ ግልጽነት የጎደለው አካሄድ መኖሩን የፋኖ አባሉ ይገልጻሉ። ይህም የመንግሥት ዓላማ ሕግ ማስከበር አይደለም የሚል የጥርጣሬ ሐሳብ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነና ከዚህ በፊት ሲናፈስ የነበረው ፋኖን ትጥቅ የማስፈታት ወሬን እውነት አስመስሎታል ይላሉ።
በፋኖ ጉዳይ በክልሉ መንግሥት ውስጥ ከላይ እስከ ታች ፋኖን በጥርጣሬ ዐይን የሚመለከቱና ፋኖን የሚደግፉ አካላት መኖራቸው ይነገራል። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገችው ሙከራ፣ የፋኖን ኃይል መጠናከር እንደ ስጋት የሚመለከቱ የመንግሥት አካላት ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መምጣቱን ነው።
አንድ ለአማራ ክልል ቅርበት ያላቸው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ስለ ጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ፣ “ፋኖ መንግሥትን የሚገዳደር ኃይል እየሆነ መጥቷል” ይላሉ። የክልሉ መንግሥት የፋኖን ጉዳይ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚመለከተው የሚገልጹት ኃላፊው፣ ከመንግሥት የራቀ የፋኖ ቡድን እንዲኖር የክልሉ መንግሥት እምብዛም ፍላጎት የለውም ይላሉ።
ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣው የፋኖ አደረጃጀት ከመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጋር የሚገዳደር ኃይል ከፈጠረ፣ የክልሉ መንግሥት የኃይል የበላይነት ይወሰድብኛል ብሎ እንደሚሰጋ ይጠቁማሉ።
የፌዴራሉም ይሁን የክልሉ መንግሥት የፋኖን በሰው ኃይልና በትጥቅ መደራጀት በተለይ የመንግሥትን ሥርዓት የሚቃወሙ የፋኖ አደረጃጀቶች ላይ ስጋቱ ከፍ ያለ ነው ይላሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሥራ ኃላፊ። በዚህም ከላይ እስከ ታች ባለው የክልሉ መዋቅር የአቋም ልዩነቶች መኖራቸውን ይናገራሉ። ይህንኑ ተከትሎ አኩርፈው የተቀመጡና በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ሆነው ለፋኖ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ከላይ እስከ ታች መፈጠራቸውን ያብራራሉ።
የክልሉ መንግሥት ከላይ እስከ ታች ባለው የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የሐሳብ አንድነት ለመፍጠር እየሞከረ ቢሆንም፣ በፋኖ ጉዳይ አሁንም የሐሳብ አንድነት የለም ሲሉ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መንግሥትን የሚቃወሙ ኃይሎች በየፊናቸው እየተደራጁ ትጥቅ ያነሱበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ ለመንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ እንደሆነና የትጥቅ ትግሎችን ማጥፋት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአንድ ወር በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ወር በፊት ለጄነራል መኮንኖች በሰጡት የሥራ መመሪያ ስለ ትጥቅ ማስፈታት በሰጡት ማብራሪያ፣ “ሸኔ፣ ገኔ፣ በኔ…ትጥቆችን ማስፈታት ያስፈልጋል። እንደዚያ ፓራላል ፎርስስ ማምከን ያስፈልጋል፣ ፓራላል ፎርስ ፖለቲካል ብቻ ነው መከላከል ያለባቸው እንጂ፣ ተቋም በሚገዳደር መንገድ መሄድ የለባቸውም” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጄነራል መኮንኖች የሰጡትን የሥራ መመሪያ በማንሳት መንግሥት በአማራ ክልል እያካሄደ ያለው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን የፋኖ አደረጃጀት ማስቆም ነው ይላሉ።
“የመንግሥት ሥጋት ከመንግሥት ወገን ሆኖ ለተመለከተው ሰው፣ አያሰጋም ማለት አይቻልም” የሚሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ፣ አሁን እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ከዚያ የመነጨ መሆኑን እንደ ግለሰብ እንደሚያምኑ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል ያለውን ስጋት ከፋኖ አደረጃጀቶች ጋር የአሳዳጅና ተሳዳጅ አካሄድ ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ በንግግር ስጋቱን ማርገብና ተቀራርቦ መሥራት ለክልሉ የተሻለ እንደሚሆን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል፣ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፋኖ አባል መንግሥት በፋኖ አደረጃጀት ላይ ስጋት እንዳለው እንደሚገነዘቡ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ መንግሥት ያለበትን ስጋት ተቀራርቦ በውይይት ላይ የተመሠረተ መተማመን ከመፍጠር ይልቅ “በሕግ ማስከበር ሥም እያሳደደ ጫካ እንድንገባ እያስገደደን ነው” ይላሉ።
መንግሥት በክልሉ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥትን እስር የሚሸሹ ወጣቶች ወደ ጫካ እየገቡ መሆኑን የሚገልጹት የፋኖ አባሉ፣ በዚህ መንገድ የክልሉን ችግር መፍታት እንደማይቻል ይጠቅሳሉ። በዚህ ወቅት መንግሥት ከፋኖ ጋር የሚያደርገው ግብ ግብ ከሚፈታው ችግር ይልቅ የሚፈጥረው ችግር እንዳይብስ መንግሥት “አፈናውን” ማቆም አለበት ይላሉ።
አዲስ ማለዳ በወልዲያ፣ በመራዊና በሽዋሮቢት አካባቢ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የፋኖ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች የመንግሥትን እስር ሸሽተው ጫካ ገብተዋል ተብሏል።
አማራ ክልል ከለውጥ ማግሥት እስከ ዛሬ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጥንት እስከ ዛሬ የሰላም አየር የራቀው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች በየጊዜው የፖለቲካ ትኩሳት የሚፈጥራቸውን ችግሮች እያነሱ ይተቹታል። “አምባገነን” ከሚባለው ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው በኢሕአዴግ የመሪነት ዘመን የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት፣ በአንድ ወገን የሥልጣን የበላይነት የሚዘወርና ወደ ዴሞክራሲ የሚያሻግር አይደለም በሚል ብዙ ትችቶችና ተቃውሞዎች ይፈጠሩበት ነበር።
ይህንኑ ተከትሎ በተለይ ከ2008 ወዲህ ተጠናክሮ በቀጠለው ተቃውሞ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀው አሁን ላይ ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ ለሚጠራው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስረከቡት። ኢትዮጵያን በወቅቱ ከነበረችበት ችግር ያሻግራሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸው የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወቅቱ ከየአቅጣጫው የሕዝብ ድጋፍና አድናቆት ጎርፎላቸው ነበር።
አማራ ክልልም የዚህ አካል የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ በነበረው ችግር ተቃውሞ ከሚሰማባቸው ክልሎች መካከል አንዱ አማራ ክልል ነበር። “የለውጥ መንግሥት” የተባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በወቅቱ በፈጠረው የኢትዮጵያዊነትና አንድነት ስሜት ከዚሁ ክልል በተደጋጋሚ በሰልፍ የተደገፈ ድጋፍና አድናቆት አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ አማራ ክልል የወቅቱን የለውጥ ስሜት በአግባቡ ሳያጣጥመው ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ መግባቱን ብዙዎች ይገልጻሉ።
ለዚህም እንደ ማሳያ የሚነሳው ሰኔ 15/2011 የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ከተገደሉ በኋላ፣ የክልሉ ፖለቲካ የተረጋጋ አለመሆኑን ነው። ክልሉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጥሩ የሚባል የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደሌለው ብዙዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
ከአምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና የሥራ ባልደረቦቻቸው መገደል በኋላ በክልሉ ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር አለመኖሩን የሚያነሱ ሰዎች፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቀስ በቀስ የክልሉ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አስተዳደር ላይ እምነት እያጣ መምጣቱን ያነሳሉ።
ክልሉ ሰኔ 15/2011 ተፈጸመ በተባለው “መፈንቅለ መንግሥት” ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አምባቸው መኮነን፣ ሌሎች የክልሉ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ከተገደሉ አንድ ወር በኋላ ከተሾሙት ከተመስገን ጥሩነህ እስከ አሁኑ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)፣ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ተፈራርቀውበታል። የአመራር መፈራረቁን በተለይ ክልሉ ላይ ትኩረት አድርገው ሐሳብ የሚሰነዝሩ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ፖለቲከኞች በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዳይፈጠር አድርጓል ሲሉ ይደመጣሉ።
ጥቅምት 24/2013 በትግራይ ክልል የተጀመረው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ወደ አማራ ክልል ተስፋፍቶ እስከ ደብረ ሲና ደርሶ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ክልሉ አስተናግዷል። አሁንም በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሕወሓት ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎች መኖራቸውን መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ አገር የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አይደለችም የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ በመንግሥት በኩል ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘበ አካሄድ እየተከተለ አለመሆኑ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትችት በርትቶበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014
“ራሱን የለውጥ መንግስት” ብሎ የሚጠሬው? Really? Secondly why didn’t you include attempts made by the GOE, religious leaders and local elders to settle the issue? From far away, i have heard about the kidnappings for ransom, lootings, jailbreaks, arms deals, rapes and murders. I understand conflict sells, but even if you are not concerned about the victims. you should be mindful that lawlessness and vigilantism may affect you and those close to you.