መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበኮንሶ ዞን በአንድ ወር ብቻ ከ26 ሰዎች በላይ በታጣቂዎች ተገድለዋል ተባለ

በኮንሶ ዞን በአንድ ወር ብቻ ከ26 ሰዎች በላይ በታጣቂዎች ተገድለዋል ተባለ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ኮንሶ ዞንና አጎራባች አካባቢዎች በአንድ ወር ብቻ ከ26 ሰዎች በላይ በማይታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ሥማቸው እንዲታወቅ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ኮንሶ ዞን ከሚያዚያ 7/2014 ጀምሮ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ፣ በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ እና በተለያዩ ቦታዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂ ኃይሎች በየወቅቱ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዳልቆሙ ባለሥልጣኑ ጠቁመዋል።

ባለፈው አንድ ወር ብቻ በታጣቂ ኃይሎች ከ26 ሰው በላይ እንደተገደለ እና ከ100 በላይ ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በየጊዜውም ታፍነው ከሚኖሩበት አካባቢ የሚወሰዱ ሰዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ ከምንጯ ሰምታለች።

በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ፣ ቡርጂ ልዩ ወረዳ፣ አሌ ልዩ ወረዳ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ በአማሮ ልዩ ወረዳ በሚፈጠሩ ጥቃቶች በተለያዩ ወረዳ እና ቀበሌ የሚኖሩ የአርሶ አደሮች ቤት እና ንብረት እየተቃጠለ ነው። እንዲሁም በኮንሶ ዞን አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም እየተፈናቀሉ እና በየጊዜው ሕይወቱን ለማዳን ሀብትና ንብረቱን በመተው ከሚኖርበት ቀዬ የሚሰደድ ሰው ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተነገረው።

ከኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ፣ በአሌ ልዩ ወረዳ ወደ አርባምንጭ ከተማ እና ሌሎች ወረዳዎች የሚወስድ የትራንስፖርት አገልግሎት ከቆመ ከአንድ ሳምንት በላይ እንዳለፈው እና ማኅበረሰቡ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንደተቸገረም ተገልጿል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ልዩ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ኃይል በዞኑ እና በተለያዩ ልዩ ወረዳዎች ተመድቦ የጸጥታ ችግሩን ለማረጋጋት የተሰማራ ቢሆንም፣ የጸጥታ ኃይሉ በማያካልላቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዳልቆሙ ተጠቁሟል።

ከሚያዝያ 18/2014 በኋላ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ከሰገን ዙሪያ ወረዳ ማዕከል ሰገን ከተማ ሰባት ሴት እና 10 ወንድ በድምሩ 17 ንጹሐን ዜጎች በታጣቂ ቡድኑ ታፍነው ወደ ሌላ አካባቢ እንደተወሰዱ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

እነዚህን ዜጎች ለማስለቀቅ የሞከረ የመንግሥት አካል አለመኖሩን ያነሱት ነዋሪዎቹ፣ በሰገን ከተማ የነበሩ የፌዴራል ፖሊስ እና ልዩ ኃይሎች ንጹሐን ዜጎች ታፍነው በተወሰዱበት ወቅት ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል በካምፕ ውስጥ እያሉ ዜጎቹን ለማስለቀቅ ጥረት አላደረጉም ተብሏል።

የደቡብ ክልል መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጣቂ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ ባለመውሰዱ ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን እያጎለበተ መሆኑንም ባለሥልጣኑ ጠቅሰዋል።

የአማሮ ልዩ ወረዳ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አማረ አክሊሉ እንደገለጹት፣ በልዩ ወረዳው እና በአጎራባች አካባቢዎች ከሚያዚያ 17/2014 ጀምሮ በየጊዜው በታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች አዲስ ማለዳ መረጃውን እስከጠየቀችበት ጊዜ ድረስ እንዳልቆመ ጠቁመዋል።

ባለፈው ሳምንት ከኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ጋላና ወረዳ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ አማሮ የተለያዩ ቀበሌዎች ዘልቀው በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውን ቡድን መሪው አስረድተዋል።

አክለውም፣ ግንቦት 10/2014 ታጣቂ ኃይሎቹ በፈጸሙት ጥቃት በትፋቴ ቀበሌ ኹለት ታዳጊ ሕጻናት እንደተገደሉ እና በተጨማሪ ከ40 በላይ ፍየሎችን ጨምሮ ሌሎች ከብቶች ተዘርፈዋል ብለዋል። ግንቦት 2/2014 ከደርባ ቀበሌ አንድ ሰው እንዲሁም ግንቦት 7/2014 በሻሮ ቀበሌ አንድ ወጣት በታጣቂዎች መገደላቸውን የጠቆሙት የቡድን መሪው፣ በአጠቃላይ ግንቦት ወር ከገባ ብቻ ከአራት በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ተናግረዋል።

የደራሼ ልዩ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ተማሪ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ በየወቅቱ የሚፈጠር የጸጥታ ችግርን ለመቅረፍ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት ተመድቦ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም፣ በየወቅቱ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዳልቆሙ ገልጸዋል።

በወረዳው እስከ አሁን ባለው ከ25 ሺሕ በላይ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ የሟቾች፣ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር የማጣራት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ለሆኑት ሠራዊት ዲባባ አዲስ ማለዳ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብታደርግም ምላሽ አላገኘችም፡፡ በተጨማሪም ለኮንሶ ዞን ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ገረሱ ካታሌ ጥያቄውን አቅርባ፣ ጥያቄውን ካደመጡ በኋላ ምላሽ ሳይሰጡ ስልካቸውን ዘግተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች