መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበኅብረት ሥራ ማኅበራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 43 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

በኅብረት ሥራ ማኅበራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 43 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለውጭ ገበያ ካቀረቡት ምርት ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በ2014 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ውጪ ተልኮ የተገኘው ገቢ ታቅዶ ከነበረው አንጻር ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ ቢኖረውም፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን ቅናሽ ማሳየቱን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አያልሰው ወርቅነህ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ከ3 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ይህም የቡና የዓለም ገበያ መዋዠቅ፣ ማር፣ እጣን እና ሙጫ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክልሎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ወደተለያዩ አገራት ይላክ የነበረው ምርት በኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የተነሳ መላክ ባለመቻሉ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ላይ ከጥራት ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮች አለመፈታታቸው ለገቢው መቀነስ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው ተብሏል።

ከሐምሌ 1/2013 እሰከ መጋቢት 30/2014 ባሉት ዘጠኝ ወራት፣ ከ24 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እንደታቀደ እና ከተቆላ ቡና 30 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሰሊጥ ወይም ከቅባት እህል ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ ከቦሎቄ ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደተገኘ እንዲሁም በአጠቃላይ ከ43 ሚሊዮን 473 ሺሕ በላይ ዶላር መገኘቱ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በተጨማሪ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዘጠነኛውን አገር ዐቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን ባዛር እና ሲምፖዚየም በማዘጋጀት የምርት አቅርቦት እንዲሁም ግብይትን በተመጣጠነ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማድረሱ ውጤት አምጥቷል ተብሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው ‹ሰንደይ ማርኬት› የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር በማድረግ የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማረጋጋት በየሳምንቱ ቅዳሜ እና እሁድ በኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎች አስተባባሪነት በ57 የሰንደይ ማርኬት ቦታዎች፤ 219 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሳትፈዉበት እስከ 150 ሺሕ ቶን የተለያዩ ምርቶችን ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል። ሸማቹ ኅብረተሰብም በኩንታል ከ300 እስከ 350 ብር ድረስ በቅናሽ እየቀረበለት ነው።

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ውጤታማነቱን በመገንዘብ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች እና የዞን ከተሞች የማስፋፋት ሥራ ያከናወነ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በሀረሪ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በሲዳማ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አገልግሎቱን ማስፋፋት መቻሉ ታውቋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በግብይት ውስጥ ሕጋዊ ያልሆኑ ደላላዎች መበራከት እና በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው ያለ አግባብ የሚሠሩ ደላላዎች መኖራቸው፣ የግብርና ምርት ዋጋ አተማመን ስርአት አለመኖሩ፣ በአምራች ሸማች መካከል ኢ-ፍታኃዊ ግብይት በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱ፣ ከፍተኛ የምግብ ጥራት ያላቸው የግብርና ምርቶች ወደ የኢንዱስትሪ ምርቶች በመቀየር ላይ በመሆናቸው ወደ ፊት የአካባቢዎችን የምግብ ዋስትና ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ መመለስ አለመቻሉ የታዩ ክፍተቶች ሲሆኑ፣ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች