መነሻ ገጽአንደበት‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር አሉታዊ አንድምታ ያለው መወቃቀስ ነው››

‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር አሉታዊ አንድምታ ያለው መወቃቀስ ነው››

በኢትዮጵያ ሴቶችና የፖለቲካ ተሳትፎ ነገር ከተነሳ ሥማቸው አብሮ ይነሳል። ደግሞ ፖለቲከኛ ብቻ አይደሉም፤ ይጽፋሉ። ‹ምርኮኛ› እና ‹ያላረፉ ነፍሶች› የተሰኙ ኹለት ታሪካዊ ልብወለድ መጻሕፍትን ለአንባቢያን አድርሰዋል፤ ቆንጂት ብርሃን።

በየልጅነት ዕድሜያቸው ነበር የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ የወጣት ሊግ አባል በመሆን የፖለቲካ ጉዞአቸውን አሃዱ ብለው የጀመሩት። በጊዜው የኢሕአፓ አባል መሆን ከጥፋቶች ሁሉ ጥፋት ሆኖ ይቆጠር ነበር፤ በዛም የተነሳ ቆንጂት የጭካኔ በትር ከወረደባቸው ወጣቶች መሀል ነበሩ። ያ እስራትና ግርፉት ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ዛሬም ድረስ የጤና እክል እንዳስከተለባቸው ቢናገሩም፣ ብዙዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት መስዋእትነት ሲከፍሉ በሕይወት የተረፉ መሆናቸውን አያይዘው ያነሳሉ።
ቆንጂት ለ40 ዓመታት በሙያቸውና በተሰማሩባቸው ዘርፎች ለአገራቸው የሚችሉትን ሁሉ ከማድረግ እንዳልተቆጠቡ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።

በ2010 በኢትዮጵያ ውስጥ በተጀመረው ለውጥ በልጅነትና በወጣትነት የሚያውቁት ኢሕአፓ ወደ አገር ተመልሶ እንደገና ለመደራጀት ያደረገውን ጥረት ተቀላቅለው ነበር። የፓርቲው መሪ ሆነው ተመርጠውም አገልግለዋል። አሁን ላይ ከፖለቲካው እንቅስቃሴ ራሳቸውን ያገለሉት ቆንጂት፣ ከፖለቲካ ሕይወት ቆይታቸው ካላቸው ልምድ ይልቁንም ከሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የሰላም እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የተነሳላቸውን ጥያቄ በመመለስ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።


እንወቃቀሳለን፤ ያኔ እንዲህ ባያደርጉ ኖሮ ይላል የዛሬው ትውልድ። የቀደመው ደግሞ አዲሱ ትውልድ ደካማ ነው ይለዋል። በትውልድ ቅብብል መካከል የተሻገረ ድክመት እንዲሁም ደግሞ ሊወራረስ ያልተቻለ ጥንካሬ የትኛው ይመስልዎታል?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ችግር አሉታዊ አንድምታ ያለው መወቃቀስ ነው። የቀደመውን ትውልድ ማራከስና መኮነን ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ አድርገው የሚወስዱ በርካቶች ናቸው። ያንን ወቅት በትክክል ለመረዳት አንዲት ጥረት ያላደረጉ፣ ራሳቸውን በዚያ ሁኔታና ዘመን ውስጥ ለማየት “እኔ ብሆን…” ብለው ራሳቸውን ያልሞገቱ አልያም ከሌሎች ጋር ለመወያየት ያልሞከሩ ሁሉ በዛሬ ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ላይ ብቻ ተመርኩዘው ያን ትውልድ በመውቀስ የተካኑ እጅግ ብዙ ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ አዲሱ ትውልድ ያን ትውልድ ለማብጠልጠልም ሆነ ለመውቀስ የሞራል ብቃት አለው ብሎ ለመመስከር እጅግ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ትናንትን በተንሸዋረረ ዕይታ በመመልከትና ወንጀሉን ሁሉ በትናንቱ ትውልድ ላይ በመዘፍዘፍ የአዲሱን ትውልድ ኃላፊነትን ያለመወጣት ሸክም ለማቅለል የሚሞከር በመሆኑ ነው። እንዲያውም ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት አስፋሪና አሳዛኝ ሁኔታ በጥቅሉ የቀደመውን ትውልድ መኮነን ከፍተኛ ሆኗል። ይህ ውንጀላ የዘመን ተጋሪነትን ብቻ ማዕከል ያደረገ እንጂ በዚያ ትውልድ መሀል የነበረውን የአመለካከት ልዩነት እንኳ ለማየት ፈቃደኝነት የጎደለው ነው።

ያ ትውልድም አዲሱን ትውልድ በደካማነት ከመፈረጅ ያለፈ ምክንያታዊነት አይታይበትም። ከግንዛቤ ውስጥ የማይካተት ጉዳይ ቢኖር አዲሱን ትውልድ ወደዚህ ዓለም ያመጣው እና የቀረጸው የቀደመው ትውልድ መሆኑ ነው። ሐሳባችን ሁሉ ራስን የመከላከልን መንገድ የተከተለ ሆኖ ዓመታት ሲያልፉ ኹለቱ ትውልዶች በቀናነት እንዲመካከሩ እና እንዲቀባበሉ የተመቻቸ ሁኔታ አልተፈጠረም።

ስለዚህም በትውልድ ቅብብል መካከል የተሻገረውን ድክመት ማጤን እና መንስኤውንም በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ያ ትውልድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፉ ከፍተኛ እልቂት ከማስከተሉ ባሻገር፣ በሕይወት የተረፉት ከፍተኛ ሥነ-ልቡናዊ ጠባሳ አትርፈዋል። እናም መስዋዕት ለሆኑ ጓደኞቻቸው ዘወትር ሀዘንተኛ ሲሆኑ፣ እነርሱን ተከትሎ የመጣው ትውልድ ጉዳት እንዳይደርስበት ከመጠበቅ አንፃር ከሁሉ ነገር (ከአገሩም ጉዳይ) ራሱን ያራቀ እንዲሆን በማድረጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በመሆኑም ከትውልድ ትውልድ ሊሸጋገር ይገባው የነበረ የዚያ ትውልድ አገር ወዳድነት፣ ለወገን የነበረው አሳቢነት፣ ለዕውቀት ይሰጥ የነበረው ቦታ፣ ለለውጥ የነበረው ፍላጎት፣ ከግል የፖለቲካ ሥልጣን ይልቅ ለአገር አሳቢነት ወዘተ ዕሴቶቹ ወደሚቀጥለው ትውልድ ሳይተላለፉ ቀርተዋል።

ብዙዎች የዚያ ትውልድ አባላት ልጆቻቸው እንኳ ስለቀደመ ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸው አንዳችም ነገር እንዳያውቁ ሲያደርጉ፣ በአንፃሩ የተለየ እሳቤ የነበራቸው የትውልዱ የዘመን ተጋሪዎች በተለይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ሚና በነበረው በኢሕአፓ ላይ ተከላካይ በሌለበት የማጠልሸቱን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ሠሩበት። ተከታዩ ትውልድም ባለማመዛዘን የወረደውን በሙሉ የተቀበለ በሚመስል መልኩ ለቀደመው ትውልድ የነበረው አመለካከት በከፍተኛ ደረጃ ተንሸዋረረ። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ለደረሰችበት የፖለቲካ ኪሣራ ሁሉ ማወራረጃው ያ ትውልድ እንዲሆን ተፈረደበት።

ሆኖም ዛሬም አልረፈደም፤ የኔ ትውልድ ኢትዮጵያ ዛሬ እየደረሰባት ያለው መከራ እንዳይደርስባት ሕወሓትን ከጅምሩ አንስቶ የታገለ መሆኑን፣ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላም ሲታገለው ዓመታት ማለፋቸውን ሕዝብ እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ያ ትውልድ ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ መገኘቱን የሚመሰክሩ ጠንካራ የዚያ ትውልድ አባላት ያስፈልጋሉ።

ሕወሓት የዚያ ትውልድ መለኪያ ያለመሆኑን ለመመስከር አንደበቶች ሊናገሩ ይገባል። በአንፃሩ ግን አዲሱ ትውልድ ደካማ ነው በሚባልባቸው ሁኔታዎች የቀደመው ትውልድ ተጠያቂነቱን መጋራት ይገባዋል። በሌላም በኩል ቆራጥና ለአገራቸው ዘብ የሚቆሙትን የአዲሱን ትውልድ አባላት ማድነቅም ያስፈልጋል። በቀና አመለካከት እነዚህ ኹለት ትውልዶች በአገራቸው ጉዳይ ሊመክሩ እና ሊዘክሩ ይገባቸዋል።

በዕርቅ እና በሠላም ሥራ ውስጥ እንደ አገር ሽማግሌ ወይም እንደ ሀይማኖት አባቶች ሁሉ፣ ሴቶች የተለየ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል ብለው ያምናሉ? ከሆነስ ምን መሆን ነው ያለበት?
በመጀመሪያ ደረጃ በዕርቅና በሠላም ድርድር ውስጥ ሴቶች ከወንዶች እኩል ሚና ሊኖራቸው ይገባል። ምናልባትም እንደ አገር ሽማግሌ ወይንም እንደሀይማኖት አባቶች በተጨማሪነት ልዩ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ሠላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ የሴቶችን አስተዋጽኦ እጅግ አስፈላጊ የሚያደርጉት ግልጽ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ሴቶች የየማኅበረሰባቸውን 50 በመቶ ቁጥር መያዛቸው በራሱ የሠላም ማስፈን ሥራውን ወንዶችና ሴቶች በጋራ እንዲሠሩት ግድ ይላል።

በተጨማሪም ሴቶች በዋናነት ቤተሰባቸውን የሚንከባከቡ በመሆናቸው እነርሱ የሌሉበት ሠላምን የማስፈን ሥራ በሁሉም ላይ ተጽእኖ ያሳርፋል። ሴቶች የሠላም ሰባኪዎች፣ ጠባቂዎች፣ እርዳታ ሰጭዎችም ናቸው። እናም እነርሱ ያልተሳተፉበት የሠላም ማስፈን ተግባር ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት በሠላም ማስፈን ሒደት ውስጥ የሴቶችን ምልከታ ለማካተት ይህን ያህል ስኬታማ የሆኑ ሥራዎች ተሠርተዋል ለማለት አያስደፍርም። የሴቶች ግጭቶችን የማስወገድ እና ሠላምን የማስፈን ተሳትፎ ስኬታማ ያልሆነባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ።

ከእነዚህም ውስጥ አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃት የሚፈጥሩት ፍርሃት ሴቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብታቸውን እንዳይጠይቁ የሚጫኑዋቸው መሆናቸው። ግጭቶች በሚፈጠሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ቤተሰባቸውን በማሸሽ እና በመንከባከብ የሚጠመዱ መሆናቸው ሠላምን በማስፈኑ ሒደት ጫና የሚፈጥርባቸው መሆኑን መመልከት የተለመደ መሆኑ እንዲሁም በየማኅበረሰቡ ያሉ ባህላዊ ተጽዕኖዎች ሴቶች ወደ አደባባይ ገፍተው እንዲወጡ ያለመፍቀዳቸው፤ አንዳንድ ለመውጣት የሚደፍሩ ሴቶች ቢኖሩ እንኳን አስፈላጊው ትምህርት ወይንም ሥልጠና ሊኖራቸው ያለመቻሉ ተሳትፎአቸውን ገድቧል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዛሬም ቢሆን ተዋናዮቹ ወንዶች መሆናቸውን መካድ አይቻልም። ቢሆንም ብዙ ተጽዕኖዎችን አሸንፈው ወደፖለቲካው መድረክ የወጡ ሴቶች የሉም ማለትም አይደለም። የእነዚህን ፖለቲከኛ ሴቶች ቁጥር እና ጥራት ከፍ ማድረግ ታዲያ እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ሴት ፖለቲከኞች ከፍተኛውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።

- ይከተሉን -Social Media

እነዚህ ሴቶች በዚህ ተግባር እንዲበረቱ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥት እና ሲቪክ ማኅበራት ሊያግዟቸው ይገባል። እገዛው በምርጫ ጊዜ ብቻ የሚከሰትና ለወራት የሚደረግ ሳይሆን ከግጭቶች በኋላ ሠላምን በዘላቂነት ለማስፈን የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ፣ የቴክኒክ እና የማደራጀት እገዛን ሊያካትት ይገባል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ሴቶችን በሚገባ ባለማሳተፉ ምን አጥቷል ማለት እንችላለን?
ሴቶችን በሚገባ ማሳተፍ ሲባል የይስሙላ ተሳትፎ ያልሆነ ማለት ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት በብቃትና በፍላጎት የሚሳተፉ ሴቶችን ባለማፍራቱ ያጣቸው እጅግ በርካታ ነገሮች አሉ። የሴቶች ተገቢ የሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ተጨባጭ የሆነ የዴሞክራሲ ትሩፋት፣ በፓርቲዎች መሀል ከፍተኛ ትብብሮችን እና ዘለቄታዊ የሆነ ሠላምን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የታመነ ነው።

ሴቶች ወደ አመራር ሲመጡ ይዘው የሚመጡት አስተዋጽኦ ማኅበረሰቡ ከሰጣቸው ከሦስቱ ሚናዎች ይመነጫል (መውለድ፣ ቤተሰብን መንከባከብ፣ ማኅበረሰባዊ ግልጋሎት መስጠት)። እነዚህ ሚናዎቻቸው ሴቶች ለነገሮች ትኩረት መስጠትን፣ መውደድን እና ማገዝን፣ ሠላማዊነትን፣ ተባባሪነትን፣ ትህትናን፣ ለሌሎች የማሰብን እና የመጨነቅን እንዲሁም ፍቅር መስጠትን እንዲላበሱ ያደርጓቸዋል። በመሆኑም ወደ አመራር ሲመጡ እነዚህን ባህሪያት ሁሉ እንደያዙ ነው። ሴቶች አገልጋይ መሪ የመሆንን ትልቅ እሴት ይዘው ይመጣሉ።

የሴቶች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የሥርአተ ፆታ እኩልነትን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲኖረው ትኩረት በሚሰጣቸው የፖሊሲ ጉዳዮች እና በመፍትሔነት የሚቀርቡ ሐሳቦችን የተለዩ ሊያደርግ መቻሉን ጥናቶችም አረጋግጠዋል። በሴቶችና በወንዶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው የፖሊሲ ጉዳዮች የተለያዩ ሲሆኑ፣ ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ ሴቶችን እና ሌሎች የተገፉ የማኅበረሰብ አባላትን ለሚያሳስቡ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆናቸው ፖሊሲዎች ለእነዚህ ጉዳዮች ምላሽ እንዲሰጡም ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

በርካታ ሴቶች ወደፖለቲካ በገቡ መጠን የሕዝብን ሕይወት ለማሻሻል ትኩረት ስለሚደረግ ቤተሰብን፣ ሴቶችን፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን፣ ጤናን እና ትምህርትን የሚመለከቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ቅድሚያውን እንደሚወስዱ በርካታ ማሳያዎች መኖራቸው እርግጥ ነው። በመሆኑም ሴቶችን በአግባቡ የሚያሳትፍ የፖለቲካ ሥርአት ሲኖር በማኅበረሰቡ፣ በተወካዮች፣ በፓርቲዎች፣ በዜጎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ በማምጣት ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ያደርጋል። ይህ የሴቶች ተሳትፎ ድህነትን በመዋጋት ረገድ ያስከተለው አዎንታዊ ለውጥ እንደሩዋንዳ ባሉ ታዳጊ ሀገሮችም መታየቱ ተመስክሯል።

የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ የመሆኑን ያህል ሴቶች አንድ ዓይነት ያለመሆናቸውንም መቀበል ያስፈልጋል። የሴቶች እድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የመኖሪያ ቦታ፣ የሕይወት ልምድ ትኩረት በሚሰጧቸው ጉዳዮችና በሚያቀርቧቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው መገንዘብም ጠቃሚ ነው። በመሆኑም ሁሉም ፖለቲከኛ ሴቶች የሴቶችን ጉዳይ አጀንዳቸው ያደርጋሉ ማለት ትክክል አይደለም።

እናም የሴቶች በፖለቲካው መድረክ መሳተፍ ብቻውን ዴሞክራሲን ለመገንባት በቂና አስተማማኝ ሁኔታ ነው ማለት አይቻልም። ይህም በሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ዙሪያ በርካታ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ መግባት እንደሚኖርባቸው ያሳየናል፤ ያም ሆነ ይህ የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ መካድ አይቻልም።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን “በርካታ ጥናቶች እንዳሳዩን ልማትን ለማምጣት ሴቶችን ከማጎልበት የተሻለ መሣሪያ የለም፤ የኢኮኖሚ ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ ወይንም የሕፃናትን እና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የተሻለ ፖሊሲ የለም፤ የአመጋገብ ሥርአትን ለማረጋገጥ እና ጤናማነትን ለማምጣት፣ የቀጣዩን ትውልድ እድል ለመፍጠር ሴቶችን ከማብቃት የተሻለ ፖሊሲ የለም” ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ሴቶችን በአግባቡ ባለማሳተፉ ያጣቸውን ነገሮች በቀላሉ ማየት ይቻላል።

- ይከተሉን -Social Media

ብዙ ጊዜ ሴቶችን ማብቃት፣ ማሠልጠን፣ ወዘተ. ሲባል ነው የምንሰማው። የመንግሥት ፖሊሲና አሠራሮች ያጎደሉትንም በሚገባ እናውቃለን። ግን ከራሳቸው ከሴቶችስ ምን ይጠበቃል? የሚጠበቅባቸውን አድርገው ነው መብታቸውን እየጠየቁ ያሉት ብለው ያምናሉ?
በመሠረታዊነት በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ እጅግ አብዛኛዎቹ ሴቶች የሚኖሩት ማኅበረሰቡ በሚጠብቅባቸው መንገድ ነው። ሴቶች ከሕፃንነታቸው ጀምረው እየሰሙ ያደጉትን ባህሪ ተላብሰው መኖራቸው ነው ሥርዓተ ፆታ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን ማኅበራዊ ነው የሚያሰኘው።
ዛሬም ቢሆን ሴት ልጅ ቆንጆ፣ ሽቅርቅር የወንድ ልጅን ቀልብ የምትስብ እንድትሆን የሚገፋፋት ባህል ተቀየረ ማለት አይቻልም። ዛሬም ከትምህርት ዓይነቶች እንዲሁም ሥራዎች የሴት እና የወንድ ተብለው የተፈረጁ መኖራቸው እርግጥ ነው። ሴቶችን ማብቃት ማሠልጠን የሚባለውም ይህንን ለመለወጥ ነው።

እንደእውነቱ ከሆነ አሁን ላይ ሴቶች በበርካታ ጉዳዮች ለውጥ እያመጡ መሆኑ አይካድም። በርካታ ሴቶችን በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ እንዲሁም በንግድ ድርጅቶች በከፍተኛ አመራርነት ብቅ ብቅ ሲሉ እየተመለከትን ነው። እኒህ ሴቶች ታዲያ የሚጠበቅባቸውን ሳያደርጉ ለዚያ ደረጃ ደረሱ ማለት አይቻልም። ብዙ እንቅፋቶችን ተቋቁመው እየወጡ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።

ይህ የጥቂት ሴቶች የመስታወቱን ጣሪያ (Glass Ceiling) ሰብረው መውጣት ታዲያ ለሌሎች አርአያ መሆንን እና ሌሎች ሴቶች ወደዚያ ደረጃ እንዲመጡ መሥራትን ይጠይቃል። ሴቶች በውሱን ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ለውጥ እንዲያመጡ ለውጡ ከራሳቸው መጀመር ይኖርበታል፤ በተለይ በፖለቲካው መስክ ለመሳተፍ የሚያሳዩትን ቀዝቃዛ መንፈስ መለወጥ ግድ ይላቸዋል። ድርጅቶችን መፍጠርና መወያየት፤ የወንዶች ክልል ተደርጎ የሚወሰደውን የፖለቲካ መድረክ መቀላቀል ግድ ይላል።

እርስዎ በፖለቲካው በሚሳተፉበት ዘመን ብዙ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች እንደነበሩ ዛሬ ላይ ሆኖ መረዳት ይቻላል። ከዚህ ከሴቶች ተሳትፎ አንጻር አሁን ላይ ምን ምቹ ሁኔታ ታዝበዋል? ያንንስ እየተጠቀመ ያለ ትውልድ ነው ያለው?
በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ሴቶች በፖለቲካው ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተሳተፉበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ለዚያ ተሳትፎ እንደመነሻ ሊጠቀስ የሚችለው የተማሪዎች ንቅናቄ መሠረታዊ አስተዋጽኦ ነበረው። በተማሪዎች ንቅናቄ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በመመረቂያ ዓመታቸው በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመድበው እንዲያስተምሩ መደረጋቸው ደግሞ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን ወደ ኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሰራጭ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበረከተ።

እነዚያ ከዩኒቨርስቲ የሚመደቡ መምህራን ደግሞ በተማሪዎቻቸው ከመደበኛ መምህራኑ የበለጠ የሚወደዱ የነበሩ ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የለውጥ አቀንቃኞችም ነበሩ። በወቅቱ የነበረው የዓለም ፖለቲካ በምሥራቅና በምዕራብ የተከፈለ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የዩኒቨርስቲ መምህራን የምሥራቁን ርዕዮተ ዓለም (ሶሻሊዝምን) የሚያራምዱ ነበሩ። ያ ወቅት ስለሴቶች እኩልነት የሚነገርበት ሲሆን በዓለም ፖለቲካ መድረክ ላይ እነክላዜትኪንን የመሳሰሉ ስማቸው የሚጠራ ሴቶች ነበሩ። እነሌኒንን የመሰሉ እውቅ ፖለቲከኞች ስለሴቶች እኩልነትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ መጎልበት በተለያዩ ጽሑፎቻቸው የሚያነሱበትም ጊዜ ነበር።

በዚያ ዓይነቱ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ነበር የኢትዮጵያ አብዮት የተቀጣጠለው፤ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ነበር የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደመመሥረት ያደገው። በፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀትን እና የመታገልን አስፈላጊነት ለኢትዮጵያ ያስተዋወቀው የመጀመሪያ ፓርቲ ኢሕአፓ ወደመድረኩ ሲወጣ ከተቀበሉት መሀል ሴቶችም በከፍተኛ ደረጃ የመሳተፍ እድል አግኝተዋል።

በዚያ ሁኔታ የተጀመረው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የኢትዮጵያን አብዮት የጠለፈው ወታደራዊ አገዛዝ የሐሳብ ልዩነት ባላቸው ወገኖች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢያሳድርም፣ የመታገያ መድረኩ እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ለውጥ ለማምጣት የተነሱትን ወጣቶች ሴቶችንም ጨምሮ የሚያስፈራ አልሆነም።

በፖለቲካ መሳተፍ ብዙ ስቃይና መከራን፣ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚዘልቅ ዋጋ መክፈልንም አስከተለ። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጭካኔ የተስተዋለበት ጊዜ ሆነ፤ ያ ሁኔታ በሕዝብ ላይ ታላቅ ፍርሀትን ፈጥሮ ሲያልፍ፣ ፖለቲካን የመጥላት እና የመራቅን አባዜን አስከትሎ “ፖለቲካን እና ኮረንቲን በሩቁ” የሚባል ብሂልን አስከትሎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከአሁንም ቆፈኑ ያልለቀቀው ሆነ። ከደርግ በኋላ የመጣው አገዛዝም ፍርሀቱን የሚያብስ እንጅ ቆፈኑን የሚቀንስ አልሆነም።

- ይከተሉን -Social Media

እነሆ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጅምር ሁኔታዎች ቢኖሩም ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ እየተንሰራፉ የመጡት ዘረኝነት፣ ሙስና፣ ግለኝነት ፖለቲካውን የበለጠ ስላበላሹት ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍን የሚያበረታታ ሁኔታ አልተፈጠረም። የዛሬዎቹ ወጣቶች ሴቶቹንም ጨምሮ ፖለቲካን የሚማሩት እንደ 1960ዎቹ በሁሉ መንገድ ሞዴል ሊሆኑ ከሚችሉ ታላላቆች ሳይሆን፣ በዘር፣ በሙስናና በግለኝነት ከተሳሠሩ የፖለቲካ ተዋናዮች በመሆኑ የብዙዎችን ቀልብ የሚገዛ አልሆነም።

በፖለቲካ መሳተፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለግል ከመጠቀም እና በአቋራጭ ከመክበር እንዲሁም ሥልጣን ከማግኘት ጋር የተያያዘ ሆነ። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው የሴቶች ሠብዕና ጋር የሚሄድ አይደለም። በመሆኑም ሴቶች ከፖለቲካው ርቀው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ መንግሥታት የሚገመገሙበት አንዱ መመዘኛ በመሆኑ ሴቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዲወጡ የማድረግ አዝማሚያዎች ቢታዩም፣ የሴቶቹ ቁጥርም እየጨመረ ቢሄድም፣ ሴቶቹ ወደዚህ ደረጃ የደረሱት በአመዛኙ በፖለቲካ ፓርቲ ውክልና እና በኮታ እንጅ በእርግጥም የሴቶችን ጉዳይ የማራመድ ርዕይን ሰንቀው አይደለም።

አንዳንድ ጥናቶች አብዛኛዎቹ ሴቶች የሴቶችን ጉዳይ ከማራመድ ይልቅ የወከላቸውን ፓርቲ ፍላጎቶችን ሲያሟሉ እንደሚስተዋሉ ይገልፃሉ። ይህ እንግዲህ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከቁጥር ያለፈ ፋይዳ ሊኖረው እንደሚገባ አመላካች ነው።

ያም ሆነ ይህ ሴቶች በየደረጃው በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ መወከላቸውና በሥራ ኃልፊነት ላይ መመደባቸው እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ እርምጃ ነው። በተጨማሪም 6ኛው አገራዊ ምርጫ በሴቶች ተሳትፎ ዙሪያ በርካታ ሥራዎች የተሠሩበት መሆኑ ለቀጣዩ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ማየት ይቻላል።

ሴቶች አሁን ባለው ምቹ ሁኔታ እና በተፈጠረው እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታዲያ በተለያዩ መንገዶች ወደ መድረክ የወጡ ሴቶች በተለይም በሲቪክ ማኅበራት እና በተባበሩት መንግሥታት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሙያ ሴቶች በዚህ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሊሠሩ ይገባቸዋል። ሴቶችን የማነቃቃትና ወደፖለቲካው እንዲቀርቡ የማስቻሉ ሥራ ከወዲሁ ሊጠናከር ይገባዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች