መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየተረሱት በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች

የተረሱት በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች

በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት እንዲሁም በኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በሚነሱ ግጭቶች ሳቢያ ከሞቱት በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሀብት ንብረታቸውን ትተው ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ እንደሚኖሩ ይታወቃል። በእንቅርት ላይ እንዲሉ፣ ከዛም ላይ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ታክለው የተፈናቃዩን ቁጥር ጨምሮታል።

ኢትዮጵያ ይህን ጊዜ እንድትሻገር የሁሉም ዜጎቿ ርብርብ ወሳኝ ቢሆንም፣ እነዚህን ተፈናቃዮች በቋሚነት ካሉበት አስጨናቂ ሕይወት እንዲላቀቁ ለማስቻል መንግሥት ዘርፈ ብዙ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው። እንዲያም ሆኖ አንዳንድ አባካቢዎች በብዛት የሚገኙ ተፈናቃዮች ‹መንግሥት ረስቶናል› የሚል ቅሬታ አላቸው።

የአዲስ ማለዳው ሳሙኤል ታዴ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ ከ21 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ተገኝቶ ሁኔታውን ቃኝቷል። በጣቢያዎቹ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታና የተፈናቃዮችን ቅሬታ፣ እንዲሁም የተለያዩ አካላት እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ በሚመለከት ካየውና ከሰማው በመነሳት የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።


መጠለያ ጣቢያው በጫጫታ የተሞላ ከመሆኑም በላይ ያሉት ሰዎች የተከዙ፣ የጠወለጉና በየጥጉ ኩርምት ብለው አንገታቸውን የደፉ ናቸው። ብቻቸውን ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱ ሕጻናት በየቦታው አሉ። በባለሙያ ዐይን የቀነጨሩ፣ የደቀቀ ሰውነት ያላቸው ሕጻናት ሲያለቅሱ ወይም ድክም ብለው ሲቧዝዙ አልያም ሻል ሲል ሲጫወቱ ይታያሉ። በርካታ አዳጊ ልጆችም አካላቸው ሲታይ በብርድ እና በፀሐይ እንዲሁም በምግብ እጥረት እጅግ የተጎሳቆለ ነው።

በርከት ያሉ ማደሪያ ክፍሎች ያሉ ሲሆን፣ አንዱ ማደሪያ ክፍል በጣም ሰፊ፣ ያልተከፋፈለ እንዲሁም ብዙ ሰዎች በመደዳ የሚተኙበት፣ እቃ የተደራረበበት እንዲሁም ምግብም የሚበስልበት ነው። በዚህ ሰፊ አዳራሽ ውስጥ ለደቂቃ እንኳን የሰላም እንቅልፍ መተኛት እንደማይቻል ክፍሉ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይገልጻሉ።

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ እንዲሁም ለልጆቻቸው ሕክምና የሚጠይቁ በርካታ እናቶች፣ አቅመ ደካሞችና ሌሎች ሰዎች የሚታዩ ሲሆን፣ የሚሰጣቸውን የእርዳታ ምግብ ለመቀበል አንድ ቦታ ላይ ተሰብስበው የሚጠባበቁ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡
በጥቅሉ በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያለው ሕይወት እጅግ ፈታኝ እና አማራጭ በማጣት ብቻ የሚኖርበት እንደሆነ ከተፈናቃች አንደበት ይሰማል፡፡

ተድላ ሰማኝ (ሥማቸው የተቀየረ) በእድሜ ገፋ ያሉ ሰው ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የልጅ ልጅ ካዩበት ምሥራቅ ወለጋ ሀብት ንብረታቸውን ትተው ከወጡ አራት ወር ሆኗቸዋል። እንዴት እንደመጡ ሲገልፁም፣ የ10 ብር መንገድ 1 ሺሕ 500 ብር ከፍለው አልፈው ከሞት አምልጠው መውጣታቸውን ያወሳሉ። ‹‹ለደረሰብን ስቃይ ሁሉ ሰበቡ ማንነት ቢሆንም፣ በመልካም ጉርብትና አብረን ብዙ ዘመን ከኖርነው ሰዎች መካከል አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ስልክ ደውሎ ቶሎ ወደ ከተማ እንድሸሽ ስለነገረኝ ነው የተረፍኩት›› ይላሉ።

‹‹ያንን ደግ ሰው አምላክ ባይሰጠኝ አሟሟቴም በእጅጉ አስከፊ ነበር የሚሆነው።›› የሚሉት ተድላ፣ ባደሩባት ከተማም ሙሉ ሌሊቱን ሲተኮስ በማደሩ ያሳለፉትን የጭንቅ ሌሊት እንደማይረሱት ነው የሚናገሩት። ‹‹በርካቶችም ከእኔ የከፋ ስቃይ ዐይተው ተርፈው የመጡ ሲሆን፣ ለአብነትም አሁን በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ካሉት ማጅራቱን በስለት/ቢላዋ አርደው ሞቷል ብለው ጥለውት ከሄዱ በኋላ እንደምንም ተነስቶ ዛሬ ከእኛ ጋር ነው›› ብለዋል። በሚዘገንን ሁኔታ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥርም በእርሳቸው ገለፃ እጅግ በርካታ ነው።

ተድላ አሁን የሚገኙት ባለቤታቸውን እና ልጆቻቸውን ይዘው በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው። አሁን ላይ ስለሚኖሩበት ሁኔታ ሲገልጹም ‹‹በዚህ ወቅት ዋናው ፍላጎታችን ምግብ ነው። የሚረዱን አካላት እስካሉ ድረስ እንኖራለን። እነሱን ያጣን ዕለት ምን እንደምንሆን አናውቅም። የምንኖርበትን ሁኔታ ለሰው ለመግለጽም አስቸጋሪ ነው። የሚሰጠንን እርዳታ ለልጆቻችን መግበን እኛ እንደነገሩ የምንውልበት ቀን በርካታ ነው። እስከመቼ በዚህ እንደምንቀጥልም የምናውቀው ነገር የለም።›› ብለዋል።

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ያሉ ጌታቸው አበባው የሚባሉ አባወራ እንዲሁ ቀድሞ ስለነበራቸው ሕይወት ሲያወሱ፣ ‹‹እኛ የተወለድነው ምሥራቅ ወለጋ ውስጥ ነው። እዚህ ያሉ ዘመዶቻችንን አናውቅም። ስንኖርም ካለው ማኅብረሰብ ጋር በአንድነት እና በፍቅር ነው። ልጆቻችንም እዚያው ተወልድው እዚያው ተምረው እዚያው የሚኖሩ ናቸው። ሆኖም በዚህ ዓመት ምን እንደታቀደብን ሳናውቅ እና ሳንዘጋጅ ለዚህ ኹሉ መከራ ተዳርገናል።›› ሲሉ ገልጸዋል።

ብዙዎች ጫካ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው መቅረታቸውን ጠቅሰውም፣ አምልጠን መውጣት የቻልነው ብዙዎቻችን መስመር ዳር የነበርን ነን ይላሉ። ችግሩ ከመከሰቱ ቀደም ብሎም ‹ገበሬዎች ናችሁ! መሣሪያ ለእናንተ ምን ይሠራላችኋል› በማለት ከወሰዱብን በኋላ፣ በሸኔና አብረውን ባደጉ ወጣቶች እንድንጠቃ በማድረግ ለዚህ የዳረጉን የወረዳና ቀበሌ አስተዳደር ጭምር ናችው በማለት ይከሳሉ።

አባወራው ‹‹ደብረ ብርሃን መጥተን መጠለያ ጣቢያ ከገባን በኋላም መንግሥት ይደርስልናል ብለን ብናስብም ዞር ብሎ አላየንም። በጎ አድራጊ ድርጅቶች ባይኖሩ ኖሮ እኛ ሳይሆን ልጆቻችን ያልቁ ነበር።›› ብለዋል።

ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ አባትም፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ የሀይማኖት መምህር ሆነው ሲያገለግሉ መኖራቸውን ያወሳሉ። በዘመናቸው ያፈሩትን ጥሪት በሙሉ ትተው ወደ ደብረ ብርሃን በመምጣት፣ በዚህ ወቅት ቤተሰቦቻቸው ጋር እጅግ አስቸጋሪ ሕይወት እያሳለፉ መሆኑንም ተናግረዋል። እርሳቸውም ‹‹ከዚህ በኋላ የመመለስ ሐሳብ የለኝም። ብሄድም ቤት ንብረቴ በመውደሙ ከዚህ የባሰ ችግር ነው የሚያጋጥመኝ።›› ብለዋል። ስለሆነም ለጊዜው ያለሥራ መቀመጥም ጥሩ ስላልሆነ ሕጻናቱን እንዳስተምር ቢፈቀድልኝ የሚል ሐሳብ አንስተዋል።

ተፈናቃዮች እስከ አሁን ከመንግሥት ምንም ዓይነት እርዳታ አልቀረበልንም ነው የሚሉት። በተለይ በእርዳታ ድርጅቶች እስከ ዛሬ እንደደረሱ ጠቁመው ሁሌም መጨረሻችን ያሳሰበናል ባይ ናቸው።

የከተማው ሕዝብ ለእነሱ እጅግ ተባባሪ እንደሆነ ደጋግመው ይገልጻሉ። ‹‹ከተማ ወጥተን የምገዛውን ነገር እኛ በጠራነው ዋጋ ይሸጡልናል። ያለማቋረጥ በየቀኑ እንጀራና ወጥ እያመጡም ይመግቡናል። ያለእነርሱ እስከዛሬም አንደርስ ነበር።›› ሲሉ ያመሰገኗቸዋል።

ተፈናቃዮች ፍላጎታቸው ምንድን ነው?
ተፈናቃዮች ከዚያ ጭንቅ ተርፈን እስከጊዜው ስለመኖራችን እንጂ ቀጣይ እጣ ፈንታችን ምን እንደሆነ አናውቀውም ሲሉ ይናገራሉ። በርከት ያሉት ይህም ሁሌ እንደሚያስጨንቃቸው አንስተው፣ ወደመጣንበት እንመለሳለን የሚል ተስፋ የለንም ነው ያሉት። ‹‹ምክንያቱም የምንመለስ ቢሆን ኖሮ መንግሥት እስከዛሬ የሚለን አንድ ነገር ይኖር ነበር። ከዚያ ይልቅ በክልሉ መንግሥት በኩል ጠግበን የኖርንበትን ጥለን እንደወጣን ተደርጎ አጀንዳ እየተደረገ ነው።›› ያሉት ጌታችው አበባው ናቸው፡፡
‹‹በዚህ መካከል መመለስ እንደሚባለው ቀላል ባይሆንም፣ ጉዳታችንን የሚረዳና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖረን መንግሥት ዋስትና የሚሆነን ከሆነ ወደነበርንበት እንመለሳለን።›› ሲሉም አክለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በተመሳሳይ ‹‹ልጆቻችን አይማሩም፤ እኛ ሥራ አንሠራም። እስከመቼ እንዲህ እንዘለቃለን?› የሚሉት ተፈናቃዮች፣ እንደ ደርግ ዘመን አካባቢውን ጸጥ ረጭ ባለ መልኩ አደብ አስገዝቶ የሚመራ አካል እስካልተፈጠር ድረስ ብንሄድም ከነበረው የባሰ እልቂት ነው የሚጠብቀን የሚል ስጋታቸውን አንስተዋል።

‹‹ስለዚህ አሁን ያለንበት ሁኔታ አስከፊ ነው። እርዳታ ሰጭ ደርጅቶችም ሰለቻቸው መሰል ከሳምንት በፊት የምግብ እርዳታው ቆሟል ማለት ይቻላል። መንግሥት ከነመፈጠራችን ረሰቶናል። እስከ አሁን ምንም ያደረገልን ነገር የለም።›› ሲሉ ምሬታቸውን ያስረዳሉ።
ከምግብ እጥረቱ በተጨማሪ በፍራሽ እጥረት የተነሳ መሬት ላይ የሚተኙ እንዲሁም በቂ ብርድ ልብስ ባለመኖሩ ሌሊት ብርድ የሚያስቸግራቸው ስለመኖራቸውም አንስተዋል። ሲታመሙ በቂ ሕክምና እንደማያገኙ ጠቅሰውም፣ የፈለጉትን መድኃኒት ማግኘት እንደማይችሉና ይህም ሌላኛው ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው በአጽንዖት ገልጸዋል።

‹‹አሁንም በየቀኑ ተፈናቃዮች ይመጣሉ። አብዛኞቹ ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ የሚመጡ ናቸው። እኛ ከመጣንበት አካባቢ አሁንም ድረስ የታፈኑ ሰዎች አሉ። አሁንም መውጫ በማጣታቸው በየቀኑ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገደሉ በርካታ ሰዎች አሉ። በዚህ ሳምንት በኹለት ቀናት ውስጥ ብቻ አንድ ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች በአውቶብስ ተጭነው ወደ መጠለያ ጣቢያው መጥተዋል።›› ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

መጠለያ ጣቢያው ከአቅም በላይ መሙላቱን ተከትሎና፣ ባለው የፍራሽና ብርድ ልብስ እጥረት የተነሳ ቅድሚያ ለአረጋውያን በመስጠት የሚከራይ ቤት ያገኙ ከተማ ተከራይተው እንዲቆዩ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የአራትና ስድስት ወር የቤት ኪራይ ክፍያ እየተሰጣቸው የሚወጡ መኖራቸውን ነው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

‹‹ስለሆነም መንግሥት አስተማማኝ ሁኔታ ፈጥሮ ወደቦታችን ይመልሰን። ካልሆነም ሥራ መሥራት ለምንችለው የሥራ ዕድል ሊያመቻችልንና ሊፈጥርልን ይገባል። በቋሚነትም ያቋቁመን።›› በማለት ጠይቀዋል።

ተያያዥ ስጋቶች
በመጠለያ ጣቢያዎች በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ መኖራቸውን ተከትሎ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ሊጋለጡ ከመቻላቸው በተጨማሪ፣ በርካታ አዳጊዎች መኖራቸው በተለይ ሴቶች ከመጠላያ ጣቢያ ወጥተው ሊጠፉ እንደሚችሉ ማሳያዎች ስለመኖራቸው ተጠቅሷል። ለአብነትም በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ በወላጅ አልባነት ተመዝግበው ከሚኖሩ ልጆች መካከል ኹለት ልጃገረዶች በጠዋት ጠፍተው ለመሄድ ሲሞክሩ ተይዘዋል። ይህም ወጣቶችና ሴቶች ወደ ከተማ ሄደው አላስፈላጊ እና ከዚህ የከፋ ሕይወት እንዲገጥማቸው ሊያደርግ ይችላል ነው የተባለው።

ትምህርት የማይማሩ ሌሎች ታዳጊዎችም ቢሆኑ አዕምሯቸው ወደ መጥፎ ነገር ሊያዘነብል እንደሚችል ነው የሚነገረው። መጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሥነልቦና ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ የታመነ ቢሆንም እንደሌለ ተመላክቷል።
ትንሽም ቢሆን ልብስ ስፌት የሚሞክሩ፣ ቀላል የሱቅ አገልግሎት የሚሰጡና ሻይና ቡና (ከመጠለያ ካምፕ ውጭ) የሚሸጡ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎችም በመሰል ሙያዎች ለመሰማራት ሐሳብ ያላቸው አሉ። ሆኖም የክህሎትና የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልገናል በማለት ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል ስለማቅረባቸው አስረድተዋል።

በአማራ ብሔራዊ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ ደረጀ ይንገሡ፣ በአሁኑ ወቅት በዞኑ 70 ሺሕ ተፈናቃይ መኖሩን ጠቅሰው፣ በደብረ ብርሃን ከተማ ቻይና ካምፕ ውስጥ ከ12 ሺሕ በላይ፣ ወይንሸት ካምፕ ከ7 ሺሕ በላይ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር ተጠግተው የሚኖሩ 2 ሺሕ ተፈናቃዮች በድምሩ ከ 21 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ይኖራሉ ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ባለፉት ወራት ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ በተለያዩ ምክንያቶች ቆሞ እንደነበር አንስተው፣ ሆኖም ግን ከተለያዩ ድጋፍ ሰጭ አካላት የሚመጡ እርዳታዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።

በደብረ ብርሃን ከተማ በተለይም በቻይና ካምፕ ውስጥ የሚገኙት የካምፑ ባለቤቶች ቻይናውያን ልቀቁልን ማለታቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (UNHCR) ከዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) እና ከፕላን አንተርናሽናል ጋር እሠራለሁ ብሎ ከከተማ አስተዳደሩ መሬት ተቀብሎ ሼድ በመሥራት እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት በተለይ ከጦርነት ጋር ተያይዞ በአፋርና አማራ ክልል ብዙ ሕዝብ መፈናቀሉን ጠቁመው፣ አብዛኛው ግን ወደ ቀዬው ተመልሷል ነው ያሉት።
በአማራ ክልልም ክልሉ ባቀረበው መረጃ መሰረት 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ድጋፍ የሚፈልግ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑም ከክልሎች ደብዳቤ ሲደርሰው በ72 ሰዓት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አሠራራችንም ከዞንና ወረዳ ሳይሆን ከክልል ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በዚህም የክልሉን ድጋፍ ጥያቄ ተከትሎ ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 17/2014 ድረስ ለክልሉ ተረጂዎች 239 ሺሕ 383 ሜትሪክ ቶን ምግብ ተልኳል ነው ያሉት። ኮሚሽኑ በባህር ዳር የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አቋቁሞም ክልሉ እየተቆጣጠረው እንደሚገኝ አመላክተዋል። በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች ‹መንግሥት ምንም ዓይነት እርዳታ አላደረገልንም› ያሉትን አስመልክቶም፣ ‹‹ያልተረዱበት ጊዜ የለም። ደግሞስ ሕዝብ ከረዳቸው ምን ይጠበቃል። ሕዝብ እኮ መንግሥት ማለት ነው፤ ዋናው እርዳታ ማግኘታቸው ነው።›› የሚል ምላሽ ሰንዝረዋል። ዛሬ እርዳታ አቅርበን ነገ ቢጠየቅ ምንም አልተደረገልንም የሚል ምላሽ ነው ያለው ሲሉም ተናግረዋል።

ኮምሽኑ ለክልል በወር አንድ ጊዜ እርዳታ እንደሚያቀርብ ገልጸውም፣ 15 ኪሎ ግራም እህል፣ 0 ነጥብ 45 ሊትር ዘይት እንዲሁም 1 ነጥብ 75 ኪሎ ጥራጥሬ ይሰጣል ብለዋል። ከተፈናቃዮች 35 በመቶ የሚሆኑት ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር እና አጥቢ ሴቶች እንዲሁም አረጋውያን ይሆናሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ወዲያውኑ አልሚ ምግብ ይላካል ሲሉ ገልጸዋል።

በአፋር ክልልም 645 ሺሕ ተፈናቃይ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ 182 ሺሕ 660 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና ለ106 ሺሕ 997 ሰዎች 31 ሺሕ 399 ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ መላኩን አስታውቀዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁ 505 ሺሕ 402 ተረጂዎች መኖራቸውንና ከዓለም ባንክ በተገኘ 331 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ለ34 ወረዳዎች እንዲሰራጭ ተልኳል ነው ያሉት። በኦሮሚያ ክልልም በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በርካታ ዜጎች ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የተፈናቃዮች መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል?
በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች ሁሉም ማለት በሚያስችል ሁኔታ ወደቀያቸው ተመልሶ ለመሄድ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው። ከዚህ በኋላ ወደዚያ መመለስ አንፈልግም የሚሉም አሉ።
ሆኖም የቡድን መሪው ደረጀ የተናገሩት ግን ተፈናቃዮች የመጡባቸው 11 የአሮሚያ ዞኖች ሰላም መሆናቸውንና ተፈናቃዮችን ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መጀመሩን ነው።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ተፈናቃዮች የነበሩበት ቦታ ሰላም መሆኑንና መመለስ እንደሚችሉ አቅጣጫ ማስቀመጡን እና ያሉበት ድረስ መጥቶ ለማወያየትም ሐሳብ እንዳለው ጠቁመዋል። በዚህም ሰላም ካልተረጋገጠባቸው ቦታዎች ከመጡ ተፈናቃዮች በስተቀር፣ በአስራ አንዱ ዞኖች ያሉ ተፋናቃዮች የሚመለሱ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ እጅግ ከባድ ነው ሲሉ አክለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ደበበ ዘውዴ በአንጻሩ፣ አሁን ላይ ተፈናቃዮችን ስለማቋቋም ማውራት ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ ነው የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮችን ስለማቋቋም ሲነሳም አራት ጉዳዮች መታሰብ አለባቸው ካሉ በኋላ፣ በመጀመሪያ በቀያቸው ትንኮሳ መቆምና ሰላም መፈጠር አለበት። ቀጥሎ ለተፈናቃዮች እርዳታ በማቅረብ የማረጋጋት ሥራ ይሠራል። የወደሙ መሠረታዊ መሠረተ ልማቶችም መገንባት አለባቸው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው መልሶ ማቋቋም የሚሠራው በማለት አብራርተዋል።

ስለሆነም፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በግጭቶች፣ በጎርፍ፣ በድርቅ እና ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተጠቃች በመሆኑ የተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋም በዚህ ወቅት ይሆናል ብሎ ማውራት ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል።
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚደርሱ ተረጂዎች መኖራቸውን መግለጹ ይታወሳል። ለዚህም 957 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ሆኖም 338 ሚሊዮን ዶላር እጥረት እንዳለበትም ጨምሮ ገልጿል።
ይህ ወቅት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉበት፣ የተገደሉበትና የሚገደሉበት፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ዋስትና ያጡበት፣ በብዙ የአገሪቱ ቦታዎች ሕግ አቅም ያጣበት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
በተለይ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች በመንግሥት በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቢገለፅም፣ ተፈናቃዮች በአንጻሩ መንግሥት ዞር ብሎ ዐይቶን አያውቅም ያደረገልንም ድጋፍ የለም ይላሉ።

እንዲሁም፣ ወደ 11 የሚደርሱ ዞኖች ተፈናቃዮችን ለመመለስ ሰላም ናቸው ቢባልም፣ በተባሉት ቦታዎች እስከ አሁን የሚገደሉና አምልጠው የሚመጡ ስለመኖራቸው ነው የሚናገሩት።
ይህ ዘገባ ከተጠናቀረ በኋላ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በድጋፍ የሚኖሩ ከ171 ሺሕ በላይ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩ ተሰምቷል። ሆኖም በደብረ ብርሃን ከተማ ባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተፈናቃዮች ምን ያህል የሚሆኑት ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ የተገለጸ ነገር የለም።


- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች