መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳመለያየት ናፋቂዎቹ የክልልነት እና ዞንነት ጥያቄዎች መብዛት አንድምታ

መለያየት ናፋቂዎቹ የክልልነት እና ዞንነት ጥያቄዎች መብዛት አንድምታ

ኢትዮጵያ የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ማስተናገድ ከጀመረች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረች ቢሆንም፣ ባለፉት አንድ ዓመታት የቀረቡትን ያህል አይሆኑም ቢባል ግን ማጋነን አይደለም። የክልልነት ጥያቄዎቹ መነሻ ምንድን ነው? የክልል አደረጃጀቱስ እንዴት መጣ? የክልሎች ሥልጣንና ኀላፊነትስ እስከምን ድረስ ነው? የፌደራልና የክልሎች ሥልጣን እና የሕግ ተገዢነት ጥያቄዎች ዙሪያ የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ምሁራንን፣ ጥናታዊ ጽሑፎችንና ሌሎች መረጃዎችን ዋቤ በማድረግ የዛሬው የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በደቡብ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልልነትና የዞንነት (ክልላዊ መንግሥት የመመሥረት እና ራስ ገዝ ዞን የመሥረት) ጥያቄዎች ተበራክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥቅምት 2011 ግጭት ተከስቶባቸው ባወያዩዋቸው የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የጉራጌና የቀቤና ማኅበረሰብ ተወካዮች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የክልልነት ጥያቄ ነበር። በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ ከተሞች የተዘጋጁ ሦስት የምክክር መድረኮች የክልልነት ጥያቄዎች ቀርበውባቸዋል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳው ውይይት በሰጡት ምላሽ፣ ለምን የክልል ጥያቄ እንዳስፈለገ፣ የክልሉ ነዋሪዎች በሁሉም ደረጃ እንዲወያዩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ደረጃም ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀው ነበር። የክልሉን እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ በውይይቱ እስካሁን ያመጣው ለውጥ በተግባር አልታየም ይላሉ።

በአካባቢው የተከሰቱ ግጭቶችንና በስፋት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎትና ሌሎች ጥያቄዎችን በቅርበት ለመስማት የክልሉ ገዥ ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንበርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሙፈሪያት ካሚል፣ በደቡብ ምዕራብ ሦስት ዞኖች በመዘዋወር ሕዝቡን ባወያዩበት ወቅት፣ በደቡብ ምዕራብ ሦስት ዞኖች ማለትም ካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። በተለይ የአስተዳዳሪዎች ብቃት ጥያቄና የአድልዖ አሠራሮች፣ የመንግሥት አገልግሎት አቅርቦትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ሲነሱ፣ በሦስቱም ዞኖች በሸካ ቴፒ፣ በካፋ ቦንጋና በቤንች ማጂ ዞን ሚዛን አማን ከተሞች በተደረጉ ውይይቶች ከተሳታፊዎች የክልልነት ጥያቄዎች ተነስተዋል። የክልልነት ጥያቄዎቹ በደቡብ ክልል በርክተው ቢታዩም በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች መኖራቸው እሙን ነው።

የክልልነት ጥያቄዎቹ መነሻ ምንድን ነው? የክልል አደረጃጀቱስ እንዴት መጣ? የክልሎች ሥልጣንና ኀላፊነትስ እስከምን ድረስ ነው? የፌደራልና የክልሎች ሥልጣን እና የሕግ ተገዢነትስ?

የፌደራሉና የክልሎች ሥልጣን
ፌደራላዊ ስርዓት በምትከተለው ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ ለኹለቱም የመንግሥት እርከኖች የሥልጣን ክፍፍል ማድረጉን የሚያስታውሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) አንቀጽ 52፣ ንዑስ አንቀጽ 3፣ የክልል መንግሥታት የራሳቸውን የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ልማት ስትራቴጂ እና ዕቅድ ማውጣት እንደሚችሉ መደንገጉን ይናገራሉ። በተለይ ለፌደራል መንግሥቱ ወይም ለኹለቱም በጋራ ተለይተው ያልተሰጡ ሥልጣኖች በሙሉ የክልሎች ሥልጣን መሆናቸውን መደንገጉ ለክልሎች የተሰጠውን ትኩረት ሊያሳይ እንደሚችልና ኹለቱ መንግሥታት በተለይ በማዕድን፣ ጋዝ፣ ነዳጅ እና ሌሎችም መስኮች ረገድ በጋራ እንዲጠቀሙ የሚደነግግ የጋራ ሥልጣን ስላላቸው በመካከላቸው የሚኖረው ሁለንተናዊ መስተጋብር ከሕገ መንግሥቱ የሚቀዳ ነው በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ክልሎች ይሄን ያህል ሥልጣንና ኀላፊነት ቢኖራቸውም አልተጠቀሙበትም የሚሉት ሲሳይ፣ ለዚህ ደግሞ ቀድመው የነበሩት የኢሕአዴግ አመራሮችና የክልሎቹን አመራሮች ተጠያቂ ቢያደርጉም በዋናነት የክልል ኀላፊዎች ችግር መሆኑን ያጎላሉ።

የሕገ መንግሥቱ መንፈስ የሚነግረን በፌደራሉ መንግሥት እና ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በእኩልነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንጂ ፌደራል መንግሥቱ የበላይ፣ ክልሎች ደሞ የበታች የሚያደርግ የእርከን ግንኙነት አለመሆኑን የሚያወሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር ሚዛኔ አባተ (ዶ/ር)፣ በመሆኑም በመካከላቸው ዘርፈ ብዙ የመንግሥታት ግንኙነት መስኮች መኖራቸውንና ጉዳዩ በርከት ያሉ እና አወዛጋቢ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ሊነሱበት የሚችል እንደሆነ ያብራራሉ። ባንፃሩ ግን የፌደራላዊ ሥርዓቱን አወቃቀር በሚመጥን ደረጃ የመንግሥታቱ መስተጋብር ሕገ መንግሥታዊ ይዘት እና የአፈፃፀሙ ሕገ መንግሥታዊነት በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን፣ ባለሥልጣናት እና ምሁራን በቂ ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም ሲሉ ይተቻሉ።

በሕገ መንግሥቱም ሆነ ሌሎች ሕጎች በኹለቱ መንግሥታት መካከል መኖር የሚገባው የትብብር ግንኙነት በግልጽ አልተቀመጠም። በጊዜ ሒደት ግን በተለምዶ ሲሠራባቸው የኖሩ ጊዚያዊ፣ ኢመደበኛ፣ ተቋማዊ ያልሆኑ እና ሕገ መንግሥታዊ መሠረትም የሌላቸው አሠራሮች መዳበራቸውን ሚዛኔ ይገልጻሉ። በተለይ በክልል እና ፌደራል መንግሥታት የተለያዩ አካላት መካከል በጋራ የትብብር መድረኮች፣ ጊዚያዊ እና ቋሚ ኮሚቴዎች፣ ስብሰባዎች፣ የደብዳቤ ልውውጦች እና በኢመደበኛ የገዥው ፓርቲ ሰንሰለት አማካኝነት የኹለትዮሽ ግንኙነቱ ሲቀላጠፍ መቆየቱን ይናገራሉ።

የፌደራሊዝም አወቃቀርና መዳከም – የክልልነት ጥያቄዎች
ፌደራሊዝም እንደየአገራቱ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ይዋቀራል፤ በዚህም የብዝኀነት ዓምድ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ሕንድ፣ ስዊዘርላንድና ናይጄርያ ብሔርን መሠረት አድርገው ማዋቀራቸውን በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር አየነው ብርሃኑ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ማኅበረሰባዊ አወቃቀር ያላት ሲዊዘርላንድ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ልዩነትን ከአንድነት ጋር ሳይነጣጠሉ ለመምራት እንዳስቻላት የገለጹት ደግሞ የፌደራሊዝም መምህር ሲሳይ ናቸው። ከዚህ በተቃርኖ ዩጎዝላቪያና አብዛኛው የኮሚኒስት አገራት በቀዘቃዛው ጦርነት ጊዜ ፌደራሊዝምን ቢከተሉም ዴሞክራሲን ከፌደራሊዝም በመነጠላቸው መፈራረሳቸውን ይታወቃል።

ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ያልተማከለ አስተዳደርን መተግበርና ግጭትን በመቻቻል፣ ልዩነትን ከአንድነት አስታርቆ ለመምራት ዓይነተኛ የፖለቲካ መሥመር እንደሆነ ከረጅም ዓመታት ግጭት በኋላ ሶማሊያና ኢራቅ መጠቀማቸውን አየነው በማሳያነት ይጠቅሳሉ። በቋንቋ መደራጀቱ ችግር እንደማይፈጥርም ስዊዘርላድን በአብነት ያነሱት ምሁሩ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ የሕዝብን ስብጥር በአቅምነት ከመጠቀም ይልቅ የየአካባቢው ቋንቋ ተናጋሪዎች ሌላውን ለማግለል መዋሉ የስህተቱ መነሻ እንደሆነም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ሲሳይ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፣ በዋነኛነት ችግሩ ብሔር ተኮር የሆነው አደረጃጀት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር አልፎ፣ እስከመገንጠል ድረስ የሚፈቅድ መሆኑ ነው ባይ ናቸው። አንቀጽ 39ኝ ንዑስ አንድን ስንመለከት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ የብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች መገንጠል መብታቸው እንደሆነ ያስቀምጣል። ይሄ አንዱ መሠረታዊ ችግር ነው ሲሉም ያክላሉ።

የክልሎቹ አደረጃጀት ብሔር ተኮር እና ቋንቋ ተኮር ስለሆነ፥ ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን እስከዛሬ ድረስ ሥራ ላይ አልዋለም እንጂ ትልቅ መሆኑን የሚያወሱት ሲሳይ፣ የፌደራል መንግሥት የክልሎች ወኪል መሆኑን ጠቅሰው፣ ስለዚህ ክልሎች ካልፈለጉ የፌደራል መንግሥቱን ማስወገድ እንደሚችሉ ያስታውሳሉ። ራሳቸውንም እስከ መገንጠል ድረስ መብት ስላላቸው በዚህ ምክንያት የፌደራል መንግሥት ክልሎችን ለመጫን ይፈራል፤ ወይም አቅም ያጣል። በተለይ ደግሞ አሁን ያለው መንግሥት በለውጥ ላይ ያለ እንደመሆኑ፥ ቀደም ሲል ሥልጣን ላይ የነበሩት ቡድኖች በማኩረፋቸው፣ ከውጭ የነበሩ አኩራፊዎችም ከውጭ መጥተው ሕዝቡን የማደናገር ሥራ እየሠሩ ስለሆነ መንግሥትም በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ስለዚህ የፌደራል መንግሥቱ ጉልበት ኖሮት ክልሎቹን እንደፈለገ ማዘዝና ማሽከርከር አይችልም ሲሉ የችግሩን መነሻ ይጠቁማሉ።

ዋናው የፌደራል አደረጃጀት የፈቀደው ሕገ መንግሥት በዋነኛነት የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ይፈቅዳል የሚሉት ሲሳይ፥ ነገር ግን የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ በክልሎች ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል መመሥረት ይችላሉ ይላሉ።

እንደ ሲሳይ አተያይ፣ አሁን በየቦታው እየተነሳ ያለው የራስን በራስ ማስተዳደር (በተለይም ክልል የመሆን ጥያቄዎች) መነሻው ይሔ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ነው ማለት ነው። ምንም ዓይነት መሥፈርት ሳያስቀምጥ በሕዝብ ብዛትም ይሁን በቆዳ ስፋት ወይም ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች አቅም፣ ሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች የመሳሰሉትን ነገሮች ግምት ውስጥ ሳያስገባ ዝም ብሎ ብቻ ብሔር ብሔረሰቦች በመሆናቸው ብቻ ቁጥራቸው ምንም ይሁን ምን ክልል መመሥረት እንደሚችሉ እንደሚፈቅድ ሲሳይ ተናግረዋል። ለአንዱ ብሔር ፈቅዶ ሌላውን ሊከለክል ስለማይችልና ለመከልከልም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ስለማይኖረው በተለይ ልኂቃኑ ሊጠቀሙበት መቻላቸውን ያወሳሉ። እናም “መሠረታዊ ችግሩ ያለው የሚመስለኝ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር የተያያዘ ነው” ሲሉም ያክላሉ።

- ይከተሉን -Social Media

ፖለቲከኛው ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት የነበረው የፌደራሊዝም አተገባበር እውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ገዥው ፓርቲ ራሱ የሚፈልገውን አቋም ከማራመድ አልፎ የሕዝቡን አስተያየት አለማድመጡን አንስተዋል። በሌላ በኩል ተቃዋሚ ኃይሎች በተገቢው ሁኔታ የማይሳተፉበት፣ በጠላትነት የተፈረጁበት ሁኔታ መኖሩ የፌደራሊዝም አተገባበሩ ችግር ላይ እንደነበር ማሳያ ነው ብለዋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት መምህር የነበሩት እና በፖለቲካ ተቺነታቸው የሚታወቁት ሥዩም ተሾመ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የእምነትና የሐሳብ ልዩነት መኖር ተፈጥሯዊ በመሆኑ ይህን የምናስተናግድበት ሒደት ጤናማ መሆን ለአገራዊ አንድነት መሠረት መሆኑን ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመንግሥት መዋቅሮች የሚያስተላልፉት መልዕክቶች በተገቢው አለመቀረፃቸው ልዩነትን ወደ ከፋፋይነት በመቀየሩ ፌደራሊዝም ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸዋል።

የፌደራል ስርዓቱ እየተዳከመ መምጣት፣ ሕግና ስርዓት ማስከበር አለመቻል፣ የክልሎች እየጎለበቱ መምጣት፣ በተለይ ደግሞ ምንም ሕጋዊ መሠረት የሌለው ልዩ ኃይል የሚባል ሠራዊት አቋቁመው፣ እስከ አፍንጫው አስታጥቀው የፌደራሉን መንግሥት ሳይቀር “ወየውልህ!” እስከ ማለት እየደረሱ መሆኑን ጠቁመው፣ በየክልሉ የሚታዩት ሕጋዊ መሠረት የላቸውም ያሏቸው ልዩ ኃይሎች ለአገር አለመረጋጋት ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ልዩ ኃይል ማነው? ሕጋዊ መሠረቱስ?
ጀማል ድሪ ሃሊስ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ሲሆኑ ገላዴ የምትባል ወረዳን ወክለው ኹለት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል። ጀማል የልዩ ፖሊስን አመሠራረት ለቢቢሲ አማርኛ ሲያስረዱ “በአካባቢው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በስፋት ይንቀሳቀስ ነበር። ይህን ኃይል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለመደምሰስ ብዙ ጥረት አድርጎ ውጤታማ መሆን አልቻለም” ይላሉ።

ጀማል እንደሚሉት ከሆነ፤ ኦብነግን ሲወጉ የነበሩት የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የአካባቢውን ቋንቋ እና ባሕል ስለማያውቁ የአማፂውን ኀይል ከሲቪሉ ሕዝብ እንኳን ለይተው ማወቅ አልተቻላቸውም ነበር።

“2007 (እ.አ.አ) ላይ ግን የክልሉን ፖለቲካዊ ምኅዳር የቀየረ ሁኔታ ተከሰተ። ኦብነግ ነዳጅ ፍለጋ ላይ ተሠማርተው የነበሩ ከ70 በላይ ቻይናውያንና በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ገደለ። በዚህም የፌደራሉ መንግሥት ኦብነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ተነሳ” በማለት ጀማል ያስታውሳሉ። ለዚህም ሁነኛ አማራጭ የነበረው በሶማሌ ክልል ችግር ሆኖ የቆዩትን ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ሥልጠና ሰጥቶና አስታጥቆ ኦብነግ ላይ ማዝመት ነበር።

ሥዩም ተሾመ ልዩ ፖሊስ የተቋቋመው ከ2007-2008 (እ.አ.አ) ባሉት ዓመታት እንደሆነ አስታውሰው “በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን መንግሥት በወቅቱ የሽብር ቡድን ብሎ የሚጠራውን ኦብነግን ለመቆጣጠር ነበር” በማለት ከጀማል ጋር ልዩ ፖሊስ ስለተመሠረተበት ምክንያት ተመሳሳይ ሐሳብ ይሰጣሉ።

ሥዩም እንደሚሉት ከሆነ ልዩ ፖሊስ ሲቋቋም በክልሉ መንግሥት እንደሚተዳደር እና ለክልሉ መንግሥት ተጠሪ የሆነ አካል ነው ተብሎ ነበር። ጨምረው በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት ድንበር ዘለል ታጣቂ ኃይልን የመከላከል ግዴታ እና ኀላፊነት ያለበት የመከላከያ ሠራዊት ነው። ስለዚህ ልዩ ፖሊስ ሊቋቋም የሚችልበት የሕግ አግባብ የለም በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በአገር መከላከያ የኢንዶክትሬኔሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጀነራል ሞሐመድ ተሰማ ግን የልዩ ፖሊስ አመሠራረት ምንም ዓይነት የሕግ ከለላ የለውም የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉም።

ሜጀር ጀነራል ሞሐመድ “ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት አለ። መደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች አሉ። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም እንደማንኛውም ክልል የልዩ ኃይል ፖሊሶችን አሠልጥኖ እና አቋቁሞ ካሠማራ በኋላ ከፌደራል ኃይል ጋር የፀጥታ ማስከበር ሥራን ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም በአካባቢው የተሻለ መረጋጋት ተፍጥሯል። ከሕጋዊ ዕውቅና ውጪ የተቋቋመ አልነበረም” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ይህ ኀይል ምንም ዓይነት የሕግ ድጋፍ የለውም የሚሉት ሲሳይ፣ ለክልሎች የተሰጠው የክልሉን ፖሊስ የማደራጀት ሥልጣን ብቻ መሆኑ እየታወቀ፣ እነርሱ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ክንፍ አድርገው ልዩ ኃይል እንደሚያደራጁ አውስተው፣ ነገር ግን ይህ ልዩ ኃይል የመከላከያን ዓይነት አደረጃጀት ያለው፣ በቡድን የሚንቀሳቀስ፣ የቡድን መሣሪያ ያለው፣ የዕለት ተዕለት ሥራው የሰላም እና ፀጥታ ማስከበር ሳይሆን ዳር ድንበር የሚጠብቅ የሚመስል ወይም ጠንከር ያለ ሁኔታ በክልሉ ሲፈጠር ወደዛ በመብረር የፈጥኖ ደራሽ ሥራን የሚሠራ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ቅርፅ ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም ሲሉ ያብራራሉ።
“የልዩ ፖሊስ አደረጃጀትን ስንመለከት በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ አይደለም ያለው። ልዩ ፖሊስ የራሱ አዛዥ አለው። አዛዥ ደግሞ ተጠሪነቱ ለቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለነበሩት አብዲ ሙሐመድ ዑመር ነበር” ይላሉ ሥዩም። አክለውም ክልሎች በራሳቸው የፈጠሯቸው እነዚህ ሠራዊቶች የሚመሩት በጄነራሎች፣ በኮሎኔሎችና በሠለጠኑ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መሆኑ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱን የሚያሰጋና የፌደራል መንግሥቱንም የሚገዳደር ስለመሆኑ ያስረዳሉ። እንደ ምሣሌም በትግራይ ክልል ሚኒሺያው በከፍተኛ የጦር መኮንን በኮሎኔል መመራቱን፣ አማራ ክልል በጄነራል፣ ኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ በጄነራል የሚመሩ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ፖለቲከኛው ግርማ እንደሚሉት ከሆነ ልዩ ፖሊስ የክልሉ ፖሊስ ውስጥም ይሁን የሚሊሻ መዋቅር ውስጥ የለም። እነዚህ ኃይሎች በከባድ መሣሪያ ታግዘው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው፣ ነገ ላይ እራሳቸውን አፈርጥመው የፌደራል መንግሥቱን ስላለመጣላቸው ምን ዋስትና አለ? ሲሉ ይጠይቃሉ።

የፌደራል መንግሥቱ በመጀመሪያ ማድረግ ያለበት ነገር የክልል ልዩ ኃይል የሚባል ነገር እንዳይኖር በአዋጅ ከልክሎ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ደግሞ ወደክልሉ ፖሊስ እንዲገቡ ማድረግ ነው የሚሉት ሲሳይ (ዶ/ር) ይህንን በፍጥነት ማስተካከል ካልተቻለ ግን እነዚህ ኃይሎች ጉልበታቸውን አፈርጥመው ለፌደራል መንግሥቱም ሆነ ለክልል መንግሥታት ስጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው ሲሉ የሚያስጠነቅቁት ደግሞ ሥዩም ናቸው።

የወቅቱ ፈተና “የሕግ የበላይነት”
የሕገ መንግሥት መምህሩ ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እየተዘጋጀ በሚቀርበው “አዲስ ወግ” በተሰኘው ውይይት ላይ፣ የሕግ የበላይነት ከስርዓትና ከይዘት አኳያ አንፃር እንደሚገለጽ በማስታወቅ፣ “የሕግ የበላይነት፣ የዜጎችንና የመንግሥትን ግንኙነት የሚመራ ስርዓት ነው። የመንግሥት ሥልጣን በሕግ መመራት አለበት፤ ዜጎችም በሕግ መመራት አለባቸው” ሲሉ ያብራራሉ።

እንደ እርሳቸው ምልከታ የሕግ የበላይነት አለ ለማለት ዘጠኝ መሥፈርቶች አሉ፣ እነሱም የሕግ የበላይነት መገለጫዎችም ናቸው ይላሉ። እነዚህም ሕግ ግልጽ የሆነ ይዘት ያለው መሆኑ፣ በሕግ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በሕግ እንጂ በውይይት የማይፈቱ መሆኑን፣ በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ነው የሚል መርህ መኖሩን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በቅንነት መተግበር ያለባቸው መሆኑን፣ መሠረታዊ መብቶችንና ነጻነቶችን ያከበረ መሆን ያለበት መሆኑን፣ የፍርድ ቤቶችን ነጻነት ማረጋገጥ ማስፈለጉን፣ የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት ማስፈለጉን፣ ሕጎችን በማስፈጸም ረገድ ወጥነት መኖሩና የፍርድ ቤቶች ሒደት ፍትሐዊ መሆን ያለበት መሆኑ ናቸው።

የሕግ የበላይነትን በተመለከተ የመንግሥት አሠራር በዘፈቀደ ሳይሆን በታወቀና በሚታመን ሕግ የሚመራ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት መዓዛ፣ ዜጎች ማንኛውንም ሕግ ቢሆን ማክበር አለባቸው ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ዜጎች የማይወዱትን ሕግ ጭምር ማክበር እንዳለባቸው በዚሁ ውይይት ላይ ያነሱት መዓዛ አሸናፊ፣ የማይወዱትን ሕግ ለማስቀየር ግን ተደራጅተው መታገል እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018 በዓለም የፍትሕ መድረክ ጥናት መሠረት ከ186 አገሮች 118ኛ ደረጃን በሕግ ማስከበር የያዘች መሆኗን፣ በግለሰቦች ነጻነት መመዘኛ ደግሞ ከ162 አገሮች 150ኛ ላይ መሠለፏን ያስታወሱት መዓዛ፣ “አሁን ያለንበት ሁኔታ ማንኛውንም መንገድ ተጠቅመን ሕግን ከማስከበር ወደ ሕግ የበላይነት መሔድ ነው ያለብን” ሲሉ አመላክተዋል።
ለዚህም ለሕግ የበላይነት ማዕከል የሆኑትን ፍርድ ቤቶች ደካማ አቋም መቀየር፣ የፍትሕ አካላቱን ነጻነት ማረጋገጥ፣ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እንደሚያስፈልጉ በመፍትሔነት አስቀምጠዋል።

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም ሌላም የተዘነጋ ትልቅ ነገር አለ ይላሉ፤ በክልሎች የሚታየው የማንአለብኝነት እንቅስቃሴ፣ የልዩ ኃይል ሠራዊቱ ችላ መባል ትልቁ መነሳት ያለበት ነገር መሆኑን ጠቅሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው እነዚህን ነገሮች ለማስተካከል አለመቻላቸው ከምን የመነጨ እንደሆነ እንደማይገባቸው ያነሳሉ።
የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ሥልጣን ተውጦ ፓራላይዝድ ሆኗል የሚሉት ግርማ በበኩላቸው፣ የፌደራል መንግሥቱ ሽባ መሆን ክልሎች አሁን እየሔዱበት ካለው የባሰ መጥፎ መንገድ ሊወስዳቸው ስለሚችል ማዕከላዊው መንግሥት መንቃት እንዳለበት ያስታውቃሉ።

የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ አንዱና ዋናው የመንግሥት ሚና ነው በማለት የጠቆሙት የሰላም ሚኒስትር ሙፈርያት፣ ይኼንን ሚና ለመወጣት መንግሥት ጠንካራ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።

የሕግ አስፈፃሚ አካላት የተቋቋሙበት ሁኔታ ሁሉን ዐቀፍ ሳይሆን ጽንፍ የያዘ እንደሆነ በመግለጽ፣ በዴሞክራሲና በመንግሥት ጠንካራነት መካከል ብዥታ መኖሩን በ“አዲስ ወግ” ውይይት ላይ አውስተዋል። ይኼንን ለማስተካከል ዛሬ እንሥራ ቢባል ሊሆን እንደማይችል በመግለጽም፣ ተቋማቱ እንዲህ የሆኑት ግን ሆን ተብሎ ሳይሆን በአሠራር ሒደት መሆኑንም አስታውቀዋል።
“የፀጥታ ኃይሉና ኅብረተሰቡ ያላቸው ግንኙነት የጥርጣሬ ነው፣ ከዚህ መውጣት ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል። ከ2006 ጀምሮ በሰፊው የታየው አመፅ የፀጥታ አስከባሪውን በሌላ ፅንፍ ላይ አስቀምጦ የሳለው መሆኑን በመግለጽ፣ “የፀጥታ መዋቅሩ ሕግን ለማስከበር የሚሸማቀቅበት ሁኔታ ነበር” ሲሉም አስታውሰዋል።

“ዴሞክራሲን እናስፍን ብለን አቋም ስንወስድ በርካታ ቧንቧዎች ናቸው የተከፈቱልን። ሕግን ለማስከበር ስንጥር ደግሞ ማሸማቀቆች አሉ። ደግሞ ጀመራቸው፣ ባሕርያቸው አይለቃቸውም ተብሏል። ሪፎርሙን ለማሳካት ረዥም ጊዜ ይጠይቃል” ሲሉ አስረድተዋል።

ከአሁን ቀደም አንፃራዊ ሰላምና ደኅንነት መኖሩን በመግለጽ መዋቅራዊ ጥንካሬ እንዳልነበረው ጠቁመው፣ አሁን እሱን ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን በዚህም ሕዝብን ለማሳተፍ እየተሞከረ እንዳለ ተናግረዋል።

በሕግ ማስከበር ሒደት መንግሥትና ሕዝብ ተደጋጋፊ እንደሆኑና ተተካኪ እንዳልሆኑ የተናገሩት የሰላም ሚኒስትሯ፣ “የሚደጋገፉበትን ጉዳይ መቀያየር ሲጀመር አደገኛ ነው የሚሆነው” ሲሉ የኃላፊነት መገፋፋትና የእሱ ነው የእኔ አይደለም ከተባለ የሚያስከትለውን ችግር ያመላክታሉ።

“ለመንግሥት በብቸኝነት የተሰጠው የጉልበትና የማስፈፀም ኃይል፣ የሰው ልጅ የተማከለ ጉልበት ከሌለ እርስ በርስ አንገት ለአንገት እየተያያዘ ይጨራረሳል ከሚል ዕሳቤ የመጣ ነው” ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እየተዘጋጀ በሚቀርበው ‘አዲስ ወግ’ በተሰኘው ውይይት ላይ የገለጹት የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በብቸኝነት የሚይዘው ኃይል የመጠቀም መብት በሕግ ተደንግጎ በሕዝብ ተቀባይነት ሊኖረው የግድ ይላል ሲሉ ያብራራሉ።

መንግሥት በየቦታው ችግሮች ሲከሰቱ የማባበል ፖለቲካን እንደሚከተል ገልጸው፣ “ማባበያ ከረሜላ እየተሰጠው ነገ አይሆንም ኬክ ነው የምፈልገው እየተባለ ማቆሚያ የሌለው አዙሪት ውስጥ እንገባለን” ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።

“ፅንፈኞች ምላስ ብቻ ሳይሆን እጃቸው ላይ ከበድ ከበድ ያለ መሣሪያ ገብቷል” በማለት ያስታወሱት መምህሩ፣ “የሕዝብ አመፅም ይሁን አብዮት ከመደብ የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን ከድክመትም ሊነሳ ይችላል። ሕዝቡ ስለተበደለ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ደካማ ከሆነ አብዮት ሊነሳ ይችላል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

እንደ መፍትሔ
በአገሪቱ ቀጣይነት ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የፌደራል መንግሥቱ በመጀመሪያ ማድረግ ያለበት፣ የፌደራል መንግሥቱንና የክልሎቹን ሥልጣን በግልጽ ማስቀመጥ፣ ሁሉም በተቀመጠለት ፍኖተ ካርታ ሕግን መሠረት አድርጎ እንዲንቀሳቀስ ማድረግና የክልል ልዩ ኃይል የሚባል ነገር እንዳይኖር በአዋጅ ከልክሎ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ደግሞ ወደክልሉ ፖሊስ እንዲገቡ ማድረግ ነው የሚሉት ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ ቀጥሎ የብሔር ተኮር የሆነውን የፌደራል አደረጃጀት በጥናት ላይ ያልተመሠረተ፣ የሰዎችን ፍላጎት፣ ነጻነትና መልካም ፈቃድ ያገናዘበ ስላልሆነ አሁን በተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን አማካኝነት እንደ አዲስ ሊሠራበት እንደሚገባ ይመክራሉ።

አንዳንድ ክልሎችም ወደ ሦስት አራት የሚከፈሉበት ነገር ቢኖር ችግር የለውም የሚሉት ሲሳይ፣ በዚህ መንገድ ያለው ትርምስ የሚቆምበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ይላሉ። በቀጣይም ደቡብ ውስጥ ሰባት ስምንት ክልሎች መውጣታቸው እንደማይቀር በመተንበይ።

“ይህንን መቀበል ነው መፍትሔው ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች። ከመቶ ሚሊየን በላይ ሕዝብ አላት፣ በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ስብጥር በጣም ትልቅ አገር ነች፤ ከ15 እስከ 20 የሚሆን ክልል ቢኖር ችግር የለውም” ሲሉም ምክራቸውን ይለግሳሉ። ትንሽ አገር የሆነችው ጣሊያን እኮ 20 ክልል ነው ያላት የሚሉት ሲሳይ፥ በጣም ትንሽ የምትባለው አውሮፓዊት አገር ስዊዘርላንድ 27 ክልል እንዳላት ጠቁመው፥ የክልልነት ጥያቄዎችን ከዚህ በኋላ በኀይል ማስቀረት እንደማይቻል፣ ይህ ካልሆነ ክልሎች አሁንም ማስቸገራቸው እንደማይቀር ያስጠነቅቃሉ።

እስካሁን የፌዴራል መንግሥት የሚመድበውን የድጎማ በጀት ለክልሎች የሚደለድልበትም ሆነ የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት የአሠራር ስርዓት ወጥነትና ቅንጅት የጎደለው በመሆኑ የተነሳ፣ በክፍፍሉ ሚዛናዊነትና ውጤታማነት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋሉ የመጡ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ መደበኛ የአሠራር ስርዓት ለመዘርጋት አዲስ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ በክልልና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባም እየተገለጸ ነው።

በተጨማሪም የክፍፍሉ ሒደት የበለጠ ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና ተጠያቂነት ይሰፍንበት ዘንድ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር በማስፈለጉ የሕግ ማዕቀፉ እንዲዘጋጅ ምክንያት መሆኑንም ረቂቁ ያስረዳል።

በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚመድበው ጥቅል ድጎማ የሚከፋፈለው፣ የክልሎችን የወጪ ፍላጎትና ዕምቅ የገቢ አቅም መሠረት በማድረግ መሆኑ ፍትሐዊ ክፍፍል መኖሩን ማሳያ ሊሆን ስለሚችል ሊበረታታ ይገባዋል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው ኹለተኛው የድጎማ ዓይነት ደግሞ፣ አንድ የተወሰነ ወይም የተገደበ ዓላማን ለማሳካት ታስቦ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ውስን ዓላማ ያለው ድጎማ የሚሰጥበት መርሕ በረቂቁ ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ወሰን ውስጥ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ለሚገቡ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ለማስፈፀም፣ በአንድ ክልል የሚሰጥ አገልግሎት በሌላ ክልል ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ምክንያት የሚያስከትለውን ወጪ ለማካካስ፣ ለዘላቂ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለማጥበብ የሚሉት ይገኙበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች