መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየቤተ መንግሥት አስተዳደርን ጨምሮ የሚወገዱ ንብረቶችን የማያስወግዱ መሥሪያ ቤቶች በጀታቸው ይቀነሳል ተባለ

የቤተ መንግሥት አስተዳደርን ጨምሮ የሚወገዱ ንብረቶችን የማያስወግዱ መሥሪያ ቤቶች በጀታቸው ይቀነሳል ተባለ

የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ማስወገድ ያለባቸውን ንብረት እስከ ቀጣዩ አንድ ወር ካላስወገዱ በጀት እስከመቀነስ የሚያስችል እርምጃ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ሊወሰድ እንደሚችል የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት መወገድ የነበረባቸው አገልግሎት የማይሰጡ፣ ከ280 ያላነሱ የቆሙ ተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ ቁርጥራጭ ብረቶች መኖራቸውን ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ በመተባበር በተሠራው ሥራ ማረጋገጥ እንደተቻለ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰጠኝ ገላን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለአብነትም የፌዴራል የመንገድ አስተዳደር በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በየአንዳንዱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከሦስት በላይ ተሽከርካሪዎች፣ ቤተ መንግሥት አስተዳደር ከኹለት በላይ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሦስት በላይ ተሽከርካሪዎች፣ አርሲ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ ከሦስት በላይ ያልተወገዱ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለውም ባለሥልጣኑ ለፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስወገድ ያለባቸውን ንብረቶች ከላይ እስከተጠቀሰው ሰኔ 30/2014 ወይም የተያዘው በጀት ዓመት ሳይጠናቀቅ እንዲያስወግዱ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። በተጠቀሰው ቀነ ገደብ ንብረቶችን ያላስወገዱ ተቋማት በቀጣይ በጀት ዓመት ከሚለቀቅላቸው በጀት ላይ መቀነስ የሚያስችል እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ገንዘብ ሚኒስቴር የተቋሙ ኃላፊዎችንም በሕግ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችልበት እድል አለ ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባለሥልጣኑ ከብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት 659 ተሽከርካሪዎች፣ በጊንጪ ከተማ 26 ተሽከርካሪዎች፣ በጫንጮ 20 ተሽከርካሪዎች እና በሆለታ 17 ተሽከርካሪዎች በድምሩ ከ722 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 176 በተሽከርካሪ ተነስተው በጨረታ እና 546 በስክራፕ መልክ ተነስተው ሊወገዱ የሚችሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ሊወገዱ ችለዋል ብለዋል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ከአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በጋራ በመሆን እየሠራ ሲሆን፣ በባለሥልጣኑ በኩል መረጃዎችን የማጣራት ሥራዎችም ይቀጥላሉ ተብሏል።

ኃላፊው አክለውም በቀጣይ ከተሽከርካሪዎች ባለፈ በስክራፕ መልክ መወገድ ከነበረባቸው ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ማሽነሪዎች፣ የጦር መሣሪያዎች እና ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በጨረታ ለብረታ ብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ እንዲተላለፉ ለማድረግ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

መሥሪያ ቤቶች የገንዘብ ጣሪያ ሳይገድባቸው ንብረቶችን በሚያስወግዱበት ወቅት የሽያጩን ሂደት አስመልክተው መሥሪያ ቤቶች ትእዛዙን በመተግበር የደረሱበትን ርቀት ለባለሥልጣኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የገበያ ዋጋ መረጃን በተመለከተም የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በማጤን እና ያለውን ክፍተት በመለየት በጨረታ መክፈቻ ዕለት ያለውን መነሻ ዋጋ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንዲጠይቁ እና መረጃውን ማግኘት ካልቻሉ እንዲሁ በጨረታ መክፈቻ ዕለት ቅርብ የሆነውን የዋጋ መረጃ እንደመነሻ እንዲወስዱ ባለሥልጣኑ ጠቁሟል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በሌላ በኩል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተቀናጅቶ መሥራት በሚቻልባቸው የኬሚካል እና አገልግሎታቸውን የጨረሱ ኤሌክትሮኒክሶች አወጋገድ ሥርዓት ዝርጋታ ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከጥቅም ውጭ የሆኑ ኬሚካሎች እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ላይ ጥንቃቄ እና ጥበቃ እንዲያደርጉ ከማድረግ ባለፈ የአሠራር ማሻሻያ ሰርኩላር እንዲደርሳቸው ተደርጎል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች