እገታና እንግልት እስከ መቼ?

0
1182

ሥሙ እንዲጠቀስ አልፈቀደም፤ ታሪኩን ግን አጫወተን። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን፣ በተለያየ ጊዜ የሚያደርገውን እገታ በተመለከተ በቤተሰቡ ላይ የደረሰውን ነገረን። ታሪኩ እንዲህ ነው፤
የባለታሪካችን ወላጅ አባት በአካባቢው አሉ ከሚባሉ ምሁራን መካከል ተጠቃሽ ነበሩ። ታዲያ ፍርድ ሲጓደል የሚመለከተውን አካል ሞጋች፤ ለሙሰኛና አጭበርባሪ የማይመቹ፤ ድሃ ሲበደል በደሉ በራሳቸው የደረሰባቸው በሚመስል መልኩ ‹የሌላው ችግር የእኔም ነው። ይህ ችግር ነገ በእኔ የማይደርስብት ምክንያት የለም› ባይ ናቸው። ተበዳይ ትኩረት እንዲለገሰውም የሚሯሯጡ ነበሩ።

ሙሉ ቤተሰቡ የሚተዳደረው የወጣቱ አባት አምርተው በሚያስገቡት የሰሊጥ፤ የበቆሎ፤ የአኩሪ አተር ምርት ነው። ልጆቻቸውም ትምህርታቸውን የሚከታተሉት፤ ሙሉ የቤተሰብ አባላት በዓላትን በደስታ የሚያሳልፉት ሙሉ ሐሳብና ጭንቀታቸውን በእኚሁ የቤቱ አባወራ ጫንቃ ላይ አሳርፈው ነው።

ታዲያ ከዕለታት በአንደኛው ቀን በሚኖሩበት ሰፈር ያልታሰበ ግርግር ተፈጠረ። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ማጥቃትና ንብረታቸውን መዝረፍ ጀመሩ።
ይህን ተከትሎም ነዋሪዎቹ ሕይወታቸውን ለማዳን እናቶች ልጆቻቸውን እያንጠለጠሉ፤ ወጣቶችና አባቶች ከፊት ከፊት በመምራት የተሻለ መንገድ እያመላከቱ ሰላም ወዳለበት አካባቢ መትመሙን ተያይዙት።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከእድሜ ዘመናቸው ሙሉ ያካበቱትን ንብረት ለማንም እየተዉ እየሸሹ ባለበት ጊዜ፤ ብዙዎች ከነተሳፈሩበት መኪናቸው እየታገቱ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ የባለታሪካችን አባትም የእገታ ዕጣ ፈንታ ደረሳቸው።
ታጣቂዎቹ አባቱን አግተው ሲወስዱት ያየው ይህ ወጣት፣ ለምን ብሎ ቢሞግትም፤ ‹ለጥያቄ ፈልገነው ነው፤ ይመለሳል› ከሚል ከአጋቾቹ አንደበት ከሚወጣ የማስተባበያ ቃል ውጭ ሌላ ምላሽ ሊገኝ ሳይቻል ቀረ።

የአባቱ መታገት ሰላሙን ነሳው፤ እናም ከአጋቾች ጋር መደራደር ጀመረ። ‹‹አባትህ እንዲፈታ ከፈለክ ብር አምጣ›› የአጋቾቹ ቀጭን ትዕዛዝ ነበር። የታጋቹ ቤተሰቦች በተፈጠረው ድንገተኛ ጥቃት ቤት ንብረታቸውን ትተው ወጥተዋል። ከኪሳቸው የነበረውን ብር መንገድ ላይ ተቀምተው ታጣቂዎቹ ሊገድሏቸው ሲሉ እናቶች ተንበርክከከው እያለቀሱ በልመና ነው ማለፍ የቻሉት።

ባለታሪኩ የሆነውንና ያሳለፈውን ለአዲስ ማለዳ መናገሩን ቀጥሏል። አባቱን ለማስፈታት ከአባቱ ወዳጆች ብድር ለመጠየቅ ወሰነ። አምጣ የተባለው 310 ሺሕ ብር ነበር። የታጋቹ ልጅ ከጓደኛ፤ ከቤተሰብ ጠያይቆ አጋቾቹ እንዲያመጣ የጠየቁትን ብር ይዞ ቀረበ።
አባቱ ስለታሰረበት አማራጭ ስላጣ እንጂ ታጣቂዎቹ ለእርሱም የማይመለሱ መሆናቸውን ያውቅ እንደነበር ያስታውሳል።

ወጣቱ በአባቱ የተጋረጠው ችግር በእርሱ ላይ እንደደረሰ እየተሰማውና ወኔ እያላበሰው ታጣቂዎቹን ቀርቦ በድፍረት አዋራቸው። ብሩን አምጥቻለሁ ግን አባቴን ስትፈቱ ነው የምሰጠው አለ።
‹‹አባትህ ይፈታል። ብሩን አምጣ፥ እኛ የምንፈልገው ብር ነው። የሚፈታው ግን ነገ ነው>> የአጋቾች ምላሽ ነበር። አማራጭ የሌለው የታጋቹ ልጅ ብሩን ሰጥቶ የአባቱን መፈታት በተስፋ መጠበቅ ጀመረ። የሆነው ግን እንደጠበቀው አይደለም። ታጣቂዎቹ ብሩን ከወሰዱ በኋላ አባቱን እንደገደሉት እንባ እየተናነቀው ይናገራል።

እንባውን ለመግታት እየሞከረም <<ምን ዋጋ አለው። ሚዲያ ሰማው አልሰማው ምን የሚመጣ ለውጥ አለ? ከዚህ በፊትም እንዲዘግቡት ተናግሬ ነበር። ግን አየር ላይ አልዋለ>> ሲል አከለ።
አስከትሎም አሁን 11 የቤተሰቡ አባላት ተፈናቅለው እንዳሉ ጠቁሞ፤ አባቱን ለማስፈታት የተበደረውን ብርም መክፈል እንዳልቻለ አንስቷል። በተጨማሪም ሙሉ እርሻ መሬታቸው ላይ የነበረው ሰብል፤ ከቤት የነበረው ንብረት በመኪና ተጭኖ እንደተወሰደና ማሳቸው አሁንም ለመታረስ ጊዜው እንዳለፈበት ነው ያመላከተው።

ስጋት
ከዓመታት ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰዎች ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለዘመናት የቆዩበትን፤ የዳሩ የኳሉበትን ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣት እየተገደዱ ነው። ከዛም በላይ በሚሸሹበት ጊዜ እየታደኑ እየታገቱና እየተገደሉ መሆኑን ይናገራሉ።
ክስተቱን የተጋሩት ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ በንፁሃን ላይ እየተፈጸመ ያለው ተግባር ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማድርግ ብቻ ሳይሆን ማገት፤ ካገቱ በኋላ ብር ማስከፈል፤ አንዳንዴም ካስከፈሉ በኋላ እንደሚገድሉ ነው።

ይህን መሰሉ ሕገ ወጥ ተግባር በይበልጥ እየተስተዋለ ያለው በተለይም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ነው። አዲስ ማለዳ በተለያዩ ወቅቶች ኦነግ ሸኔ የሚሰነዝረውን ጥቃት በማስመልከት የዘገበች ሲሆን፤ በዚህም በተለይም የጊዳ አያና የሊሙ ወረዳ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቀው ወደ ጉትን ከተማ እንደተፈናቀሉና በርካታ ሰዎች እየታገቱ እንደሚገደሉ ነው ማወቅ የተቻለው።

ከሞት የተረፉት ከ40 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በአንገር ጉትን ከተማ ተፈናቅለው የነበሩ ሲሆን፤ ሰሞኑን ወደየ ቤታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ቢጀመርም ተመላሾችም ብልጽግና ደጋፊ ናችሁ እየተባሉ እየታገቱ ብር ለመክፍል እየተገደዱ ነው ተብሏል።
እስከ አሁን የጊዳ አያና ወረዳ ተፈናቃዮች ናቸው መመለስ የጀመሩት የሚሉት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ተፈናቃይ፤ <<እስከ አሁን ግፍ ሲደርስበት የነበረው የአማራ ተወላጅ ነው። አሁን ግን የኦሮሚያ ተወላጆችም እየተሰቃዩ ነው>> ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አስከትለውም፤ ሰሞኑን ከመፈናቀል የተመለሱ 17 ሰዎች የብልጽግና ደጋፊ ናችሁ ተብለው በሸኔዎች እንደታገቱ መረጃው አለኝ ሲሉ ጠቁመው፤ ታጋቾቹም ለመውጣት እስከ 300 እና አራት መቶ ሺሕ ብር ክፈሉ እየተባሉ ነው ብለዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ሰዎችን ማገትና ብር ማስከፍል የተጀመረው ከዓመታት በፊት ነው።

ሌላኛው የሊሙ ወረዳ ተፈናቃይ <<ንብረቱን ሲያወጣ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የተያዘና ሙሉ ንብረቱን ተቀምቶ እስር ቤት ከገባ ዓመት ያስቆጠረ፣ እስከ አሁንም ያልተፈታ ሰው አውቃለሁ>> ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደሚሉት ከሆነ፤ ታጋቹ ለመታገት ያደረሰው ጉዳይ የራሱን ንብረት ይዞ ሰላም ወዳለበት አካባቢ መጓዙ ሲሆን፤ ጭኖት የነበረው ከ600 ሺሕ በላይ የሚገመት ንብረት ተወርሶበት እርሱም ታስሯል።

ባለቤቱ እርሱን ለማስፈታት ቢሄዱም 400 ሺሕ ብር ክፈሉ ተብለው መክፍል ስላልቻሉ አሁንም እንደታገተ ነው ብለዋል። የአዲስ ማለዳ ምንጭ ባብራሩት መሰረት፤ እስከ አሁን ማንነትን መሰረት ባደረገው ጥቃት በርካታ ሰዎች ታግተው የተገደሉ ሲሆን፤ ከመፈናቀል ተመለሱ የተባሉ ሰዎችም ተመሳሳይ ከስተት እያስተናገዱ መሆኑን ተከትሎ እንደገና ለመፈናቀል መገደዳቸውን ነው ያስረዱት።

አስከትለውም በጊዳ አያና ወረዳ መንደር አራትና አምስት የነበሩና በጉትን ተፈናቅለው የቆዩ ሰዎች ሰሞኑን ከመፈናቀል የተመለሱ ቢሆንም፤ ቀድሞ የነበረው ጥቃት ባለመቆሙ በድጋሚ እየተፈናቀሉ ነው ብለዋል።

ሌላኛው የሊሙ ወረዳ ነዋሪ መንደር ስድስት ብቻ ሰባት ሰዎች ታግተው እንደነበርና ግማሾቹ ብር ክፈሉ ከተባሉ በኋላ እንደተገደሉ ሌሎቹ ደግሞ ብር እንዳልከፈሉና አድራሻቸው እንደማይታወቅ ነው ያብራሩት።
አክለውም <<ብር ከፈልክም አልከፈልክም ከታገትክ አማራጭህ መሞት ነው። ታግተው የመለቀቅ እድል የሚያገኙት ጥቀቂቶች ናቸው>> ነው ያሉት።

በሕግ ሲዳሰስ
በኢትዮጵያ በርካታ የተደነገጉ ሕጎች እንዳሉ ይታመናል። ምንም እንኳ ማንም ሰው ወንጀል ሠርቶ በሕግ ከመቀጣቱ በፊት መልካሙንና ክፉውን የሚለይ ሕሊናውን ተጠቅሞ ከወንጀል ነጻ የመሆን እድል ቢኖረውም ይህን ላደረገ አካል ደግሞ በሕግ ይቀጣ ዘንድ በየፈርጁ የረቀቁ ሕጎች አሉ።

በርካቶች እንደሚሉትና በተለያዩ ቦታዎች እንደሚስተዋለው ከሆነ ግን በተለይም ከዓመታት ወዲህ ዜጎች ሕግን በሚጥሱና ከሕግ በላይ በሆኑ አካላት በተደጋጋሚ ግፍ እንደሚደረስባቸው ነው የሚናገሩት።
የዘርፉ ምሁራንም ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጡ፤ እንኳን በሰላም የተቀመጠ ሰው ወንጀል የሠራ ሰውም ሕጉ በሚለው መመሪያ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል እንጂ አግቶ መግደልና ብር ማስከፈል ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን ነው የሚያስገነዝቡት።
ለግል ጥቅም፤ ለፖለቲካ ቡድን፤ ለባለሥልጣናት እንዲሁም ለመሳሰሉት ዓላማዎች መሳካት ሰውን አሳልፎ መስጠት ሕግን መተላለፍ ነው የሚሉት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ ናቸው።

ማንኛውም ሰው በነጻነት የመንቀሳቀስና በሕይወት የመኖር መብት እንዳሏቸው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፤ የመንቀሳቀስና በሕይወት የመኖር መብትን የጣሱ ሰዎችን ቅጣትን በተመለከተ ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ በዝርዝር ተቀምጧል ነው ያሉት የሕግ ባለሙያው።
መጥለፍን በተመለከተ በኢትዮጵያ የወንጅል ሕግ ድንጋጌ መሰረት የራሱ የሆነ ቅጣት አለው ያሉት ካፒታል፤ አንድን ሰው በዛቻ፤ በማታለል ወይም በሌላ መሰል ቅድመ ሁኔታ የጠለፈ አካል የሰባት ዓመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 594 ተቀምጧል ብለዋል።

ጠለፋው የተከናወነው ሴት ላይ ከሆነ ደግም ቅጣቱ እንደሚጨምርና ከሦስት እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 6/87 ተደንግጓል ሲሉ አክለዋል።

ብሔራዊ ምክክር – ለመፍትሄ መገኘት
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የሰላም መናጋት ተከትሎ የተለያዩ አካላት ቡድናዊ ወይም ግለሰባዊ አቅዳቸውን ለማሳካት ሰዎችን የሚያግቱበት ሁኔታ አለ የሚሉት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ሱራፌል ጌታነህ ናቸው።
ሱራፌል በተለይም በፍቅረ ንዋይ ምርኮ የተያዙ ሰዎች ለአገርና ለሕዝብ የሚሆን አጀንዳና ዓላማ የላቸውም ብለው፤ ዋና ዓላማቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ማግኘት ነውና ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ግለሰቦችን ያፍናሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወንጀል ተብለው ከተጠቀሱት ድርጊቶች መካከል አንዱ መሆኑን ያብራሩት የፖለቲካ መምህሩ፤ ለዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት መንስኤው በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት፣ የሕግ መላላትና መንግሥት ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቶ አለመሥራቱ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ገፈቱን ቀምሰው መሰል ችግር እንዳይገጥማቸው እየተፍገመገሙና ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ የሚለፍፉት በርካታ ሰዎች በሰጡት አስተያየት፤ እስከ አሁን በደረሰባቸው ጥቃት ብቻ ሳይሆን በቀጣይም መሰል ድርጊት እንዳይሰነዘርባቸው ያደረባቸውን ስጋት ነው።
ይህን በተመለከተም የፖለቲካ መምህሩ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ፤ ተቋማት ተገንብተው የጸጥታ ኃይሉ ሥራውን በአግባቡ መሥራት እንዳለበት ነው ምክራቸውን የለገሱት።

ሱራፌል በተያያዘም፤ የዜጎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት በሕገ መንግሥቱ ማስመጥ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚህ ሕግ <በላይ> ሆነው ጥቃት የሚያደርሱ አካላትንም በሕግ መጠየቅ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን መንግሥት መዘንጋት የለበትም ሲሉም አሳስበዋል።
<<ይለብንን ችግር በራሳችንን መፍታት ያለብን ራሳችን ነን>> ያሉት ሱራፌል፤ በምዕራብ አፍሪካም ከዚህ የበለጠ ችግር ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፣ ምዕራባዊያኑ ግን በመወያየት እንደፈቱት ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚከተሉት ፖለቲካ የከሰረ ፖለቲካ ነው ሲሉ የተናገሩት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ ፖለቲከኞች <<ሌሎች ያሉትን ቢሉ ኢትዮጵያ መርከባችን እንደሆነችና መርከባችን ከሰጠመች ደግሞ ማንም መኖር እንደማይችል በማመን ሕዝቡ እርስ በእርሱ መዋደድ አለበት>> ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በሌላ በኩል ቸግሩን ለመቅረፍ ከምንም በላይ የብሔር ምክክር ማድረጉ አማራጭ የማይሻና ነገ ዛሬ ተብሎ ቀጠሮ ሊሰጠው የማገባ ጉዳይ መሆኑን ነው ምሁሩ የሚናገሩት።
ነዋሪዎቹ በበኩላቸው የመፍትሄ ሐሳብን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ መንግሥት የኦነግ ግብረ አበር የሆኑ አመራሮችን ለይቶ ሊያውቅና ሥራቸውን ሊከታታል እንደሚገባ ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ ሊቀረፍ እንደማይችል ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here