መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበአማሮ ልዩ ወረዳ ያለው የፀጥታ ችግር ከዞኑና ከክልሉ አቅም በላይ ነው ተባለ

በአማሮ ልዩ ወረዳ ያለው የፀጥታ ችግር ከዞኑና ከክልሉ አቅም በላይ ነው ተባለ

በኮንሶ ዞን አማሮ ልዩ ወረዳ እና በአጎራባች አካባቢዎች በየወቅቱ የሚፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ከዞኑና ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን የአማሮ ወረዳ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን አማሮ ልዩ ወረዳ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች እና በድንበር በሚያዋስነው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጅ ዞን በየወቅቱ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ከወረዳ፣ ከዞን፣ ከክልል የፖሊስ፣ የልዩ ኃይልን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ አስከባሪ አካላትን በማቀናጀት የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ነው።

ነገር ግን በአካባቢው በየወቅቱ ማንነታቸው በማይታወቁ ኃይሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚፈጠሩ ጥቃቶች እና የሰላም መደፍረሶችን ከወረዳው፣ ከዞኑ እንዲሁም ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዳልተቻለ እና በየወቅቱ ግጭቶች እያገረሹ መሆናቸውን የአማሮ ወረዳ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አማረ አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ አስቀድሞም ሚሊዮን ማቴዎስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ከነበሩበት ወቅት ጀምሮ የተጠየቀ ቢሆንም፣ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናከረችበት ጊዜ ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ ቡድን መሪው ጠቁመዋል።

ከሰኔ 7/2009 ጀምሮ እስከ መጋቢት 30/2014 ባለፉት አምስት ዓመታት በታጣቂ ኃይሎች 221 ሰዎች እንደሞቱ እና 235 ሰዎች ላይ እንዲሁ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሳቸው ቡድን መሪው ተናግረዋል።

በተጨማሪ ከ2009 ጀምሮ እስከተያዘው ዓመት ድረስ በየወቅቱ በተነሱ የሰላም መደፍረሶች ከ44 ሺሕ በላይ ሰዎ ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያ እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ተጠልለው የሚኖሩ ዜጎች አሉ ያሉት ቡድን መሪው፣ ለእነርሱም በሦስት ወይም በአራት ወር 15 ኪሎ ስንዴ ድጋፍ የሚደረግ ቢሆንም፣ ሰብአዊ ድጋፉ ግን በቂ አይደለም ብለዋል።

ቡድን መሪው አክለውም የፌዴራል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ከማሰማራት በተጨማሪ ሌሎች የመፍትሄ አማራጮችን በማስቀመጥ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራባቸው ጠይቀዋል።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግሮች በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማምጣት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሥራ ጀምሮ እንደነበር አይዘነጋም።

የአማሮ ልዩ ወረዳ ከምዕራብ ጉጂ ጋር ከሚዋሰንባቸው ቆላማ አካባቢዎች ከ2009 ጀምሮ ባሉት ግጭቶች እና ጥቃቶች ሳቢያ እስከ አሁን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው አመቺ ባልሆኑ መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነው።

ይህም አካባቢውን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በመዳረግ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።

በዚህ በሚያዝያ ወር ላይ የከብቶ ዝርፊያ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ እንደሆነና የሰው ሕይወት መጥፋት ሪፖርት እንደሌለ ጠቅሰው፣ ከአንድ ወር በፊት ግን በተለያዩ ቀበሌዎች አራት አርሶ አደሮች ሕይወታቸው የጠፋ ሲሆን በርካታ ከብቶች መዘረፋቸውን ገልጸዋል። በአማሮ የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙንና እንደ ልብ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም አስረድተዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪው የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክልና እንዲያግዝ፣ ችግር ላይ ለሚገኘው ለአካባቢው ነዋሪ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና ተጎጂዎችም ድጋፍ ተደርጎላቸው ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች