መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳ‹በዓላትን የሚጠብቁ› የድጋፍ እጆች!

‹በዓላትን የሚጠብቁ› የድጋፍ እጆች!

‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም› ከሚባሉ ለሰው ልጆች ከታደሉ ጸጋዎች መካከል የተቸገረን መርዳት ተጠቃሽ ነው። ይህም አንዱ ያለውን ለሌለው ለሌላው የማካፈል ስርዓት ነው። ይህን ለማድረግ ታድያ ልዩ የሚባሉ ወቅቶችና ሁኔታዎች ሲጠበቁ ይስተዋላል። ከዚህ መካከልም የበዓላት ሰሞን ተጠቃሽ ናቸው።

የበዓላት ሰሞን ድጋፎች ከወትሮው ለየት ያሉና በመጠንም በርከት የሚሉ እንደሆኑ ይገመታል። ምንም እንኳ በዚህ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ባይገኙም፣ በአዘቦት ቀን ከሚደረጉ ድጋፎች አንጻር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ለዚህም በቅርቡ በኢትዮጵያ የተጀመረው የማዕድ ማጋራት መሰናዶ ማሳያ ነው። ነገር ግን በዓል ተጠብቆ የሚደረግን ድጋፍ የማይደግፉ አሉ። ከዛም አልፎ ለዕይታ የሚደረጉ ድጋፎችንም ብዙዎች ይኮንናሉ። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ በጎ አድራጎት ሥራ ላይ ያሉ ተቋማትን፣ የተለያዩ ሰዎችን በማናገርና የተለያዩ ዕይታዎችን በማተት የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

የረመዳን ጾም አንድ ወር አስቆጥሮ ወደ መጠናቀቁ ቀርቧል። የኢድ አልፈጥር በዓልም ሽር ጉድ ተጀምሮለታል። የእስልምና እምነት ተከታዮች በእምነቱ አስተምህሮና ስርዓት መሠረት ክብደት ከሚሰጡት የጾም ወቅት መካከል ሲሆን፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ እርስ በእርስ መደጋገፍ እንዲሁም አንዱ ሌላውን ማገዝና መርዳት ላይ ብርታት የሚታይበትም ሰሞን ነው።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድም በተመሳሳይ ክብደት የሚሰጠው የዐቢይ ጾም ባሳለፍነው ሳምንት መጠናቀቁ ይታወሳል። ያንን ተከትሎም በሀይማኖቱ የበዓላት ሁሉ ራስ የሚባለው የትንሣኤ በዓል ተከብሮ አልፏል።
ከእነዚህ ሀይማኖታዊ አጽዋማትና በዓላት ጋር ተያይዞም በኹለቱም ሀይማኖት ውስጥ የሚገኙ የየእምነቱ ተከታዮች በበጎ አድራጎትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከጾሙና ከበዓሉ በረከትን ለማግኘት ይለማመናሉ።

እነዚህ አጽዋማትንና በዓላትን ጠብቀው የሚታዩ ተግባራት በራሳቸው ትልቅ ዋጋ ያላቸው መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን አንዳንዶች ዘንድ ደግሞ ቅሬታ ይነሳባቸዋል። ይህም ‹ለምን ሆኑ፣ ለምን ተደረጉ?› የሚል ሳይሆን፤ ለምን በአዘቦቱም ልምድ ሆነው አይዘልቁም የሚል ነው። የተቸገሩ ሰዎች የሚርባቸው ለበዓል እለት ብቻ አይደለም ወይም የታመሙ ጠያቂ የሚሹት በተመሳሳይ የጾምና የበዓላት እለት ብቻ አይደለም።

በአንጻሩ ‹የለም! ሁሌማ ድጋፍ ከተደረገ የተረጂነት ስሜት ተፈጥሮ ሁሉንም ተጧሪ ያደርጋል!› ብለው የሚሞግቱ አሉ። እናም በዘላቂነት መደጋገፍ ቢታሰብ እንኳ፣ የተረጂነትን መንፈስ የሚያጸናና በማንኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የተቸገሩ ሰዎችን በራሳቸው ከመሥራት በሚያግዳቸው መንገድ ሊሆን እንደማይገባ ያሳስባሉ።

ይህቺንም አያሳጣን!
‹ይመስገን ነው! ይህቺንም አያሳጣን። ይህንንም ያላገኘ ስንት አለ!› ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን በምስጋና ጀመሩ፤ ፈትያ አወል። ፈትያ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ነዋሪ ናቸው። ዝቅተኛ የሚባል የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ኹለት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ከምንም በላይና በጣም የሚያሳስባቸው፤ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

እንዲህ የበዓላት ሰሞን የሚደረግላቸውና ከተለያዩ አካላት የሚመጣላቸውን ድጋፍ በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው፤ ‹ይህቺንም አያሳጣን!› ሲሉ በምኞት አዘል ተማጽኖ ነው ምላሽ የሰጡት።

ፈትያ የየእለት ኑሮአቸውን ለመግፋት በልብስ አጠባና በተመላላሽነት የተለያዩ የግለሰብ ቤቶች አገልግሎት ይሰጣሉ። በዚህ የሚገኘው ገቢ ግን የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ልጆችን አስተምሮና የየእለት የምግብ ወጪን ሸፍኖ ለመዝለቅ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ይገልጻሉ።
‹‹ሁሌም እጅን መዘርጋትና ከሰው መጠበቅ ከባድ ነው። በተለይ አሁን ላይ በየቦታው ብዙ የተቸገረና ከቤቱ የተፈናቀለ ሰው ስመለከት፣ እኔ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሆንኩኝ አምኜ የባሰ ለቸገረው ድጋፍ ቢሰጥ ብዬ እመኛለሁ። ጊዜው እንዳንተሳሰብና እንዳንረዳዳ የሚያደርግ ዓይነት ነው። ያም ሆኖ ግን ያንን አልፈው ካላቸው ላይ ቀንሰው የሚሰጡንን ሰዎች፣ በዓልን ብቻ ለምን ትጠብቃላችሁ ብዬ አልወቅስም። ይህም ቀላል ነገር አይደለም።›› ሲሉም የሚሰማቸውን ስሜት ተናግረዋል።

ያም ሆኖ ግን ድጋፎች በዓልን ከማክበርና ጾም ከማስፈታት አልፈው፣ ባይሆን ጠርቀም ብለው ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ቢደረጉ ይላሉ። ይህም አነስተኛ በሚባል ወጪ ሊጀመሩ ለሚችሉ ሥራዎች መነሻ ሊሆን እንደሚችልም ዕይታቸውን ያስቀምጣሉ። ያም ሆኖ ግን ‹ይህቺንም አታሳጣን› እያሉ ደጋግመው ምኞት አዘል ተማጽኖ ያቀርባሉ።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጭር የቆይታ ደቂቃዎች ለንግግራቸውና ለሚሰጡት ሐሳብ አብዝተው የሚጠነቀቁት ፈትያ፣ ‹‹መቼም ይሁን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሰዎች ስለሚሰጡት ድጋፍ ተቀባይ ማመስገን አለበት። እኔ ሁሌም ተረጂ መሆንን አልፈልግም። ለዛም ነው በተለያየ ጊዜ በትንሽ በትንሹ የሚረዱኝ ሰዎች የዛሬ ዓመትም በተመሳሳይ እንዲረዱኝ የማልጠብቅ እንድሆን አንድ ቋሚ ለውጥ የሚያመጣ ነገር ቢደረግ የምለው። እንጂ ስለሁሉም አመሠግናለሁ።›› አጥብቀው አመስግነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ ማለዳ የአንደበት አምድ እንግዳች የነበሩት የነህምያ ኦቲዝም ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ራሔል አባይነህ በተወሰነ መልኩ የፈትያን ሐሳብ ይጋራሉ። በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ እንደተናገሩት፣ እርሳቸውም እርዳታንና ድጋፍን ለማድረግ ወቅትን በተለይም በዓላትን መጠበቅ ባይኖር ጥሩ ነበር ባይ ናቸው። ነገር ግን አንድ ጉዳይ ላይ ጊዜንና ትኩረትን ጨምሮ የመሰጠት (Commitment) ልምድ የሌለ በመሆኑ፣ በዓላትና አጽዋማትን የመሰሉ ምክንያቶች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ዕይታቸውን አካፍለዋል።

‹‹ለመርዳትም ለማገዝም ምክንያት እንፈልጋለን። ይህ በኹለቱም የሀይማኖት ተቋማት በሚገኙ ምዕመናን ላይ (በክርስትና እና እስልምና) ይስተዋላል። በጾም ሰሞንና በዓላት ሲደርሱ ድጋፍ ይጨምራል። ባይሆን [ወቅትና ሁኔታን ባንጠብቅ] ጥሩ ነበር። ከሆነም ግን ምክንያትም ተፈጥሮም ቢሆን ሌሎችን መርዳትና ማገዝ አለብን።›› ብለዋል።

ለምን?
በዓላትን ወይም ልዩ ሁኔታዎችን መነሻ አድርጎ ድጋፍ ማድረግ አልያም እርዳታ መስጠት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃም የታወቀ የሰዎች ልማድ ነው። ይህን የተረዱ አንዳንድ አገራት እንደውም የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በተለያየ መልክ ቀርጸው ሰዎች በተመቻቸውና በለመዱት መልክ እንዲሳተፉበት ለማስቻል ጥረት ያደርጋሉ።

ለምሳሌ በኢትዮጵያም አሁን ላይ እየተለመደ ያለው በሞባይል አጭር የጽሑፍ መልዕክት ቋሚ ድጋፍ ማድረግ አልፎም በበይነ መረብ የሚደረጉ የድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው። ለእነዚህም ድንገተኛ አደጋዎችና ወቅታዊ ችግሮች በዋናነት ምክንያት ሲሆኑ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በሚያደርጉት ቅስቀሳ ልክ እርዳታና ድጋፎች ይሰበሰባሉ።

ታድያ በተለይ ሀይማኖታዊ ይዘት ባላቸው በዓላት ላይ መንፈሳዊ በረከትን ለማግኘት፣ አልፎም ፍቅርንና ደስታን ለማካፈል ነው፤ ሰዎች በተለየ ስሜት ድጋፎችን የሚያደርጉት። ከፍተኛ የሚባሉ ድጋፎችና እርዳታዎች የሚደረጉትም ጾም ባለባቸውና በዓላት በሚከበሩባቸው ሰሞናት እንደሆነ መላምቶች ይሰጣሉ። ያ ለምን ሆነ?

- ይከተሉን -Social Media

በሳንዲያጎ ዩኒቨርሲቲ በሥነልቦና የትምህርት ዘርፍ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ዋያንት እንደሚሉት፣ ሰዎች በበዓላት ሰሞን ድጋፍና እርዳታን የሚያደርጉት ከሚሰማቸው ጥልቅ ስሜት በመነሳት ነው። ይህም ማለት ድጋፍ የሚሰጡት እንደው በድንገተኛ ውሳኔ ወይም ስሜታዊ ሆነው አይደለም።

እንደውም አብዛኛው ርህራሄ የሚታይበት እንደሆነው ነው ያመላከቱት። አንድ ሰው የሌላውን ወይም የተቸገረውን ሰው ስሜት መረዳት ሲችልና ለዛም ሰው በጎ ማሰብ ሲጀምር፣ በጎ ምላሽን ይቀበላል። ይህም የበለጠ በጎ እንዲሆንና እንዲለግስ ምክንያት ይሆነዋል ይላሉ። ይህም መንፈሳዊነትና ራስን በሌሎች ጫማ አድርጎ የማሰቡ ሁኔታ ከመንፈሳዊነት የሚመነጭ መሆኑ ይታመናል።

ሀናን ማህሙድ የባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የአዲስ ማለዳ የአንደበት እንግዳ መሆናቸውን ተከትሎ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥ የሆነ ጥያቄ ተነስቶላቸዋል። እርሳቸው በተለይ ከእስልምና እምነት ጋር በማያያዝ እንዳስረዱት፣ በረመዳን ጾም የሚገኘው በረከት ብዙና ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ ብዙዎች በዚህ ወቅት ድጋፍ ማድረግን እንደሚመርጡ ጠቅሰዋል።

‹‹በሀይማኖታችን መሠረት በዓመት አንድ ጊዜ ዘካ እናወጣለን። ይህንንም ብዙዎች በረመዳን ጾም ሰሞን ነው የሚያወጡት። ግን ከዛ ውጪም ይቻላል።›› ሲሉ ይጠቅሳሉ። ያም እንዳለ ሆኖ ከዛም ውጪ ግን ብንረዳዳ ጥሩ ነው ሲሉ መክረዋል።

ሀናን በሐዘን ስሜት እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ፤ ‹‹አሁን እኛ ጋር [ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት] በቀን 140 ሰው ሊመዘገብ ይመጣል፤ ድጋፍ ለማግኘት። ይህ እኛ ይህን ድርጅት ከከፈትን በኋላ በቀን የሚመጣ ከፍተኛ ቁጥር ነው። ሰዎች በኢኮኖሚ በጣም ተቸግረዋል። ደሞዛቸው ሦስት/አራት ሺሕ የሆነ ሰዎች ሳይቀር ከመሥሪያ ቤት አጽፈው እርዳታ ጥየቃ ይመጣሉ። እና በጣም ያሳዝናል።››

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት አስተያየት ሰጪዎች በሙሉ ባነሱት ሐሳብ ውስጥ፣ ሁኔታዎችን በተለይም በዓላትና ሀይማኖታዊ ክዋኔዎችን ምክንያት አድርገው የሚደረጉ ድጋፎችን አልኮነኑም። ምክንያቱም የራሳቸው ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው፣ ለሰዎች መንፈሳዊ እርካታን የሚያስገኙ እንደሆነም ያምናሉ። ነገር ግን የመስጠት፣ ካለን ላይ የማካፈል ልምድ በአዘቦቱም ሊኖር እንደሚገባ ነው የሚጠይቁት።

ፕሮፌሰር ጄምስ ዋያንት ሰዎች ለመንፈሳዊ እርካታ፣ በረከትን ለማግኘት ከዛም ከፍ ሲል ምንም ሳይጠብቁ መስጠት ያለውን ዋጋ ለመረዳት የሚያስችል ልኅቀት ላይ ሲደርሱ ብቻ አይደለም ድጋፍ የሚደርጉት ይላሉ። አንዳንዴ በለጋሾች ስም ዝርዝር ውስጥ የራሳቸውን ሥም ማስመዝገብና ተመዝግቦ ማየት ዋጋ እንዳለው የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ ነው እኚህ የሥነልቦና ባለሞያ የሚያስረዱት።

እንደውም እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ አሁን ላይ በስፋት የሚታዩት በበይነ መረብ የሚካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያዎች ውጤታማነት ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሰዎች በድብቅ በግላቸው ከሚሰጡት በላይ በብዙዎች ፊትና በአደባባይ የሚሰጡት ይበልጣል።

- ይከተሉን -Social Media

እጅ ሲሰጥ ካሜራ አይመልከት!
ሰዎች በድብቅ በግላቸው ከሚሰጡት በላይ በብዙዎች ፊትና በአደባባይ የሚሰጡት ይበልጣል የሚለው የሥነልቦና ባለሞያ ሐሳብ እውነት ይመስላል። ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚድያው በስፋት ሲንሸራሸር ከታየ ሐሳብ መካከልም አንዱ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። ድጋፍ አድራጊዎች በግል እንዲሁም በመንግሥት ደረጃ፣ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ችግረኞች ስጦታ ሲሰጡ በፎቶ አስቀርተው ብዙዎች እንዲመለከቱት አልፎም የመገናኛ ብዙኀን ዜና ሆነው መውጣታቸውን የተመለከተ ነው።

ፈትያ ይህን በሚመለከት ምን ሐሳብ እንዳላቸው አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። ‹ሰዎች እርዳታ ሲሰጥዎ ፎቶ ቢያነስዎት ምን ይሰማዎታል?› የሚል ጥያቄ ነበር። እርሳቸውም ሲመልሱ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ደስ አይለኝም። በተለይ አንዳንዶቹ ፈጽሞ ፈቃዴንም አይጠይቁም። ግን ተቸግሬም፣ የሰጪዎችን ፍላጎት አልቀበልም ብዬም አይሆንም። ስለዚህ እንዳሉኝ እሆናለሁ። አንዳንዶች ግን ፈቃዳችንን ጠይቀው ነው ፎቶ የሚያነሱትም ሆነ የሚቀርጹን።›› ሲሉ ጠቅለል ያለ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ለነገራችን መነሻ የሆነን ሀይማኖታዊ በዓል እንደመሆኑ ነገሩን ከዛው እናያይዘው። በሀይማኖቶች ‹ቀኝ እጅህ ሲሰጥ ግራ እጅህ አይይ› የሚልና ተያያዝ ቃል እስኪነገር ድረስ፣ ሰዎች ለተቸገሩ ድጋፍ ሲያደርጉ በአደባባይ አውጥቶ ማሳወቅ እንደማያስፈልጋቸው የሚያሳስብ ትምህርት አለ። ቀድሞ በነበረው ብሂልም ጎረቤቶችም ሲረዳዱ ደበቅ አድርገው፣ ገንዘብ ሲሰጡም ጨበጥ አድርገውና ሸሽገው ነው። ይህም ለራሳቸው የተለየ ክብር እንዳያገኙ በማሰብ ብቻ ሳይሆን ድጋፍ የሚያደርጉለት ሰውንም ጭምር በማክበር ነው።

አሁን ላይ ግን ይህ በፍጹም እንደማይስተዋል ነው፣ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ልጆችን የሚረዱ እናት ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት። እንደ እኚህ እናት ገለጻ፣ ለሌሎች ምሳሌ መሆን አስፈላጊ ነው። ይህም ግን የተረጂዎች ፎቶ በማይታይበትና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

‹‹ዛሬ የምንረዳቸው ሰዎች ሁሌም እዚህ እየተረዱ አይገኙም። ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሳቸው አይቀርም። እነርሱ ችግር የለም እያሉ እርዳታውን ለማግኘት ሲሉ ፈቃደኛ ቢሆኑ እንኳ ድጋፍ ሰጪዎች ግን በጣም መጠንቀቅ አለባቸው። አሁን ላይ ቴክኖሎጂ ስላለና ኢንተርኔቱም መረጃን በቶሎ ስለሚያዳርስ፣ ማን ለምን እንደሚጠቀምበት እንኳ ማወቅ አይቻልም።›› በማለት በበኩላቸው ዕይታቸውን አካፍለዋል።

ስለዚህ
የባሁል ኸይር ሥራ አስኪያጅ ሀናን መሐሙድ በበኩላቸው፤ ሰው ዓመቱን ሙሉ ነው የሚመገበው ይላሉ። በዓልን ጠብቆ የሚደረግ ድጋፍም ትክክል ነው ብለው እንደማያስቡ ነው የጠቀሱት። ‹‹ሰው ባቡል ኸይር ወይም ድርጅት ሄዶ ብቻ ይዘይር ማለቴ አይደለም። ይልቁንም ጎረቤቱን ይርዳ።›› ብለዋል።

‹‹የቅርብ ዘመድና ጎረቤቱ ተርቦና ተቸግሮ እርሱ በደኅና ሲኖር ይታያል። እንደ አገር እያጣን ያለነው ነገር አለ፣ ይህም ለሰዎች ማዘን ነው። ለቅርብ ዘመዶቻችን ሳይቀር ማዘን ትተናል። የቅርባችን የሆኑ አክስት፣ አጎት፣ ወንድም፣ እህት ወይም ጎረቤት ምን ላይ ነው ያሉት የሚለውን ማየት አለብን። በቅርባችን ያለውን ቤተሰብ ልንረዳ ይቻላል። ደኅና ኑሮ የሚኖሩ እህት ወንድም እያላቸው እርዳታ ፍለጋ እኛ ጋር የሚመጡ ሰዎች አሉ። ይህ መሆን አልነበረበትም።›› ሲሉም ቁጭትም መልዕክትም አስተላልፈዋል።

የነህምያ ኦቲዝም ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ራሔል አባይነህ በበኩላቸው፤ ሁሌም ካለን ላይ ማካፈል የሚባለውን ብናውቅ ሲሉ መክረዋል። ‹‹አንደኛ በማካፈል ማንም ሰው ከስሮ አያውቅም። ምክንያቱም ለሁላችንም ብድራትን የሚመልስ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ የሚታጣ ነገር የለም። በማካፈል ውስጥ ያለውን በረከት፣ ጤና እና ሰላም ሁሉም ሰው ቢያውቀው ብዬ አስባለሁ። ሰጥቶ የሚከስር ሰው የለም።›› ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በጎ አድራጎትና ሰዎችን መደገፍና መርዳት በገንዘብ አልያም ምግብ በማቅረብ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ይልቁንም የተለያዩ ድጋፍ ማድረጊያ መንገዶች አሉ። ይህም አሁን ላይ እጅግ ብዙ በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ ስፍራው ለመውጣት የተገደደ ተፈናቃይ፣ በዝናብ እጥረት ሳቢያ ተቸግሮ ያለ ዜጋ፣ የኑሮ ውድነት ዳዴውን ያደናቀፈበት የከተማ መሀል ነዋሪና የመሳሰለው እጅግ በርካታ ነው። እናም በገንዘብና በዓይነት ብቻ ሳይሆን ጊዜንና ሐሳብን በመስጠት ጭምር ድጋፍ ይደረጋል።

ለምሳሌ በዓላትን ጠብቆ የሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማት ጋር ምግብ ይዞ ከማቅናት ባሻገር፣ በአዘቦቱም በነዛው ተቋማት ያሉትን ሕጻናት በማጫወት፣ ትምህርታቸውን በማስጠናት፣ የሚቸግራቸውን በመጠየቅ መደገፍ ይቻላል። ተፈናቃይ በብዛት በሚገኝባቸው መጠለያዎችም በአዘቦቱ ጎራ ብሎ ‹እያሰብናችሁ ነው!› ማለት ተገቢ ይሆናል።

በመጨረሻ ፈትያ የሚሉት ካለ ሐሳባቸውን ጠየቅናቸው። እርሳቸውም ‹ተመልካችን ሳይፈልጉ፣ ፎቶ አንሱን ንገሩልን ሳይሉ ለችግራችን የሚደርሱ ወገኖች አሉ። ከበዓላት ባሻገርም የሚጎበኙን ጥቂትም ቢሆኑ አሉ። ከተማ ሆነን ለብቻችን ልጆችን ለምናሳድግ ብቻ ሳይሆን፣ ከቤታቸው ተፈናቅለው እየተንገላቱ ላሉ ሁሉ ሳያቋርጡ ድጋፍ የሚሰጡና አለን የሚሉ ሰዎች አሉ። አገራችንን ሰላም ያድርግልን፤ ለሁሉም ደግሞ ፈጣሪ ውለታቸውን ይክፈልልን!›› በማለት እንደእርሳቸው ድጋፍ በሚያገኙ ሰዎች ሥም ምስጋና እንድታቀርብላቸው አዲስ ማለዳን አደራ ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች