“ኤች አር 6600” ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

0
696

በቅርቡ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የነበረው የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ሊያጸድቀው ይችላል የተባለው ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ ነው። ረቂቁ በርከት ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን በመያዝ በ12 አንቀጾች የተዘጋጀ ነው።

ረቂቅ የሕግ ዐዋጁ ‹‹በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለመደገፍ የታሰበ፣ የንጹኃን መሞት እንዲቆም፣ የጦር ወንጀሎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የዘር ማጥፋት እና ሌሎች በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲቆሙ የሚያግዝ›› መሆኑን ያትታል።

ረቂቅ ሕጉ በተጨማሪም የዲፕሎማሲ፣ ልማትና ሕጋዊ መንገዶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሠላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው የተባለ ሲሆን፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና በጦር ወንጀል የተሳተፉት ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ኹሉንም ያካተተ አገራዊ ምክክር እንዲደረግም ይረዳል የሚል ይዘትም ተካቶበታል።

በተረፈም ረቂቅ ሕጉ ወደ አሜሪካ ለሚጓዙ ዜጎች የቪዛ ዕገዳ እንደሚያደርግ የሚገልጽ ሲሆን፣ በተለይም አንቀጽ 5 ላይ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ድጋፍ እንዳታገኝ ይከለክላል። አንቀጽ 6 እና 7 ላይም እንዲሁ በአሜሪካ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቋረጥ ብሎም ሌሎች አገራትንም በማስተባበር ብድርና ድጋፎች እንዳታገኝ የሚያደርግ መሆኑንም ይጠቅሳል።

ብዙዎች ረቂቁ ኢትዮጵያን ከዓለም የተገለለች እና በኹሉም ዘርፍ ደካማ ለማድረግ በባይደን አስተዳደር በኩል የተሸረበ፣ ከአሜሪካ አገራትን የማፈራረስ መጥፎ ልማድ ማሳያ አንዱ ነው ሲሉ እያወገዙት ይገኛሉ።
በአንጻሩ ማዕቀቡ የመንግሥት አካላት ላይ ያነጣጠረ መሆኑንና ይህም እየታዬ ያለው አስከፊ አገራዊ ችግር እንዲስተካከል እና የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ይረዳል። የአምባገነን መንግሥት ካቴና ነውና መጽደቅ አለበት የሚሉ አካላትም አሉ።

የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አንዷለም በእውቀቱ በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ረቂቁ እንዲፀድቅ ሳይሆን እዚህ ደረጃ መድረሱ እንደሚያበሳጫቸው ገልጸው፣ ከወረራ የማይተናነስ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ ከፍተኛ አደጋ ነው ብለውታል። ከላይ ሲያዩት ጠቃሚ የሚመስል ቢሆንም፣ ነገር ግን አሜሪካ የፈለገችውን አካል ለማሰርና አጀንዳዋን ለማስጠበቅ የምትጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነም ነው ያመላከቱት።

‹‹አማፂን መቆጣጠርና የውስጥ ሠላምን ማስጠበቅ የራስ አጀንዳ ነበር መሆን ያለበት። አሜሪካውያን ግን ይህን እኛ ነን የምንወስነው እያሉ ነው። ረቂቁ አገራዊ ምክክር መጀመር አለባችሁ ይላል። ይህም ከሉዓላዊነት አንጻር ካየነው ኢትዮጵያ በራሷ ጊዜ እንጂ የአሜሪካ ምክር ቤት አልነበረም የሚወስነው።›› ሲሉ አብራርተዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ይህ ሕግ እንዳይጸድቅ ያላደረገችው የለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ የመሔድ አዝማማያ ስላሳየች አሜሪካ በአንድ አገር ጉዳይ ላይ እኔ ነኝ የምወስነው በማለት ግፊት እያደረገች ነው።›› የሚል ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል።

ዐዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችንና ሌሎች ሕጎችን እንደሚጠቀም ረቂቁ ይገልጻል የሚሉት ባለሙያው፣ በሰብዓዊ መብቶች ሥም ኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰውን ጫና የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባለባቸው አገራት ላይ ስታደርገው አይታይም ብለዋል። ለአብነትም ምርጫ መደረግ ቀርቶ የምርጫ ሐሳብም ሆነ የዴሞክራሲ ፍንጭ የላትም ያሏትን ሳዑዲ አረቢያን አንስተው፣ አሜሪካ ከዚህች አገር ጋር በተቃራኒው ጥሩ ግንኙነት እንዳላት አመላክተዋል።

‹‹ኤች አር 6600›› አሜሪካ በሰዎችና በአገራት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የራሷን ፍላጎት ለማሳካት የምትሔድበትን ርቀት የሚያሳይ ነው። እስከዛሬ ከወጡ የማዕቀብ ዐዋጆች ኹሉ በኹሉም ረገድ መጥፎና ምናልባትም በታሪክ ከታዩት ኹሉ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ጨምረው አስገንዝበዋል።

ይህ ረቂቅ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንደሆነ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው። ከሠላሳ ዓመት በላይ ተዳክማና ተንኮታኩታ እንድትኖር የሚያደርግ አደገኛ ረቂቅ መሆኑንም ነው ምሁራን የሚገልጹት።
የሕግ ባለሙያው አንዷለምም ረቂቅ ሕጉ ተፈጻሚነቱን ለማሳካት በዜጎች የውጭ ጉዞ፣ በፀጥታ እና በዋናነት በኢኮኖሚው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም አደገኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ አሜሪካ በኢትዮጵያ በቀጥታ መዋዕለ ንዋይ እንዳታፈስ ይከለክላል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳታደርግ ያደርጋል። ሌሎች አገራትንም በማስተባበር ኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳታገኝ ያደርጋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ አባል ከሆነችባቸው ዓለም ዐቀፍ ታላላቅ ተቋማት ድጋፍ እንዳታገኝ አሜሪካ ያላትን ሚና ተጠቅማ እንደምትሠራ ረቂቁ ላይ መቀመጡን ባለሙያው አብራርተዋል።

አሜሪካ በዓለም ባንክ 22 በመቶ፣ በዓለም ዐቀፉ የገንዘብ አበዳሪ ተቋም (IMF) ውስጥም 17 በመቶ ድርሻ እንዳላት አንስተው፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሊያደርግ ቢያስብ ያላትን 22 በመቶ አቅም ተጠቅማ ውደቅ እንደምታደርገው ነው ያሳዩት። በዚህም ከራሷም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከዓለም ዐቀፍ ተቋማትና ሌሎች አገራት የምታገኘውን ድጋፍ እንደሚያሳጣት ተናግረዋል።

ለወደብና ድንበር ላይ ጥበቃዎች የሚሆን ዕርዳታ ካልሆነ በስተቀር፣ ለፌዴራልና ክልል የጸጥታ ኃይሎች የሚሆኑ ዕርዳታዎችም ይቋረጣሉ። ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከወዳጅ አገራት መሣሪያ እና ሌሎች ወታደራዊ ድጋፎችን እንዳታገኝ የሚያደርግ ከሆነ፣ አንዲት አገር ያለመሣሪያ እንዴት ሰላሟን ማስጠበቅ ትችላለች ሲሉ ጠይቀዋል።

ድጋፍ የሚኖረው ለመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና በዓለም ጤና ድርጅት የተረጋገጡና ለዓለም ሥጋት ለሆኑ ወረርሽኝ በሽታዎች ብቻ ነው ያሉት ባለሙያው፣ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ለምሳሌ የሚተዳደሩት ከአሜሪካ በሚያገኙት ድጋፍ በመሆኑ ይህ ከተቋረጠ አደጋ ነው ብለዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ድርጅት (NATO) አባል አገራትንም ይህን ረቂቅ እንዲደግፉ የሚመለከተው የአሜሪካ መሥሪያ ቤት ሥራውን እንዲሠራ በረቂቁ ላይ ተቀምጧል። ባለሙያው ይህን ጠቅሰው፣ የኔቶ አባል አገራት ብዛት ሳያንስ የአፍሪካና አውሮፓ ኅብረት አባል አገራትና ሌሎችንም ያካትታል ነው ያሉት። ይህም ኢትዮጵያን የሚያንኮታኩት ጥልቅ ማዕቀብ ነው ሲሉ ገልጸዉታል።

‹‹ብዙዎቻችን አሜሪካ ለሰብዓዊ መብቶችና ለዴሞክራሲ ትጨነቃለች የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አለን›› የሚሉት የሕግ ባለሞያውና ጠበቃው አንዷለም፣ ኢትዮጵያውያን ይህን ዐዋጅ ለመደገፍ ምንም ምክንያት የለንም የሚል አቋም አላቸው። ‹‹መንግሥትን መቃወም ሊኖር ይችላል። ኤች አር 6600 የሚያመጣው ጫና ግን በታሪክ ተከስቶ የማያውቅ ሊሆን ይችላል።›› ሲሉ አሳስበዋል።

ረቂቁን የሚደግፉ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ?
በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣን ውጫዊ ጫና ለመመከት እንደሚደረገው እንደወትሮው እንቅስቃሴ ኹሉ ‹‹ኤች አር 6600›› እንዳይጸድቅ ለመቃወም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አናሳ ናቸው የሚሉ አሉ። ይህም ባሉ አስተዳደራዊ ድክመቶች በዜጎች ላይ በሚደርሰው ስቃይ መንግሥትን በመቃወም እንደሆነ እና በሌላ መልኩም በረቂቁ የተነሳ ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ካለመረዳት የመነጨ እንደሆነም የሚጠቅሱ በርካቶች ናቸው።

ሆኖም እንደ አንድ ሉዓላዊት አገር የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት እንጂ ለውጭ ጣልቃ ገብነት ራስን አሳልፎ መስጠት ትርፉ የዘመናዊ ቅኝ ግዛት ሰላባ መሆን ነው በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ የሚያሰሙ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውም ዕሙን ነው።
ነገር ግን፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በደቡብ አላግባብ በየቀኑ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ መንግሥት ማስቆም እስካልቻለ ድረስ ይህ ረቂቅ መንግሥት ተጠያቂ እንዲሆንና የዜጎች ደኅንነትም እንዲረጋገጥ ይረዳል የሚሉ ኃይሎች አሉ። ለአብነት የሚያነሱትም በረቂቁ አንቀጽ 10 ላይ 90 ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች፣ የኤርትራ ኃይሎች፣ የሕወሓት ኃይሎችና ሌሎች የታጠቁ ተዋናዮች በዜጎች መብት ጥሰት እና በግድያ ተሳትፈው እንደሆነ ይጣራል ይላል።

ይህም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብተው ለዜጎች ሞትና መፈናቀል መንስኤ የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ይረዳል የሚሉ ባለተስፋዎች ብዙ ናቸው። ረቂቁ መርማሪ አካላት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙና የዘር ማጥፋት የፈጸሙ አካላትን በመለየት ለፍርድ ያቀርባል የሚል ሲሆን፣ በአገሪቱ ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦት ለማቅረብ በሚሞከርበት ወቅት መንግሥት ያስተጓጎለ ወይም ጥቃት የፈጸመ እንደሆነም ዓለም ዐቀፍ የአደጋ ጊዜ ኃይልን በመጠቀም ዕርምጃ እንደሚወሰድበት አብሮ ሠፍሯል።

ይህን በመያዝም ማዕቀቡ የኢትዮጵያዊያንን የየቀን መከራ ሊያሳጥር ይችላል በማለት ብዙዎች ሲደግፉት ይታያል። ቀደም ብሎ ከጋምቢያ፣ ኬንያና አሜሪካ የተወከሉ ሦስት መርማሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የተፈጸሙ ወንጀሎችን መርምረው እንዲያቀርቡ ቢላኩም፣ በኢትዮጵያ በኩል ፈቃድ ባለማግኘታቸው ናይሮቢ ቢሮ ከፍተው መረጃዎችን በመሰብሰብ እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል። ይህም የሆነው መንግሥት በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘግናኝ ግፎች እንዳይታዩበት ፈልጎ ስለከለከለ ነው የሚል ዕይታም በተለያየ አጋጣሚ ይሰማል።

በዜጎች ስቃይ የሚጫወቱ የመንግሥት አካላት ሳይወዱ በግድ ሥርዓት እንዲይዙ ያደርጋል፤ የዘር ፖለቲካውን ተጽዕኖም ይቀንሳል የሚል ዕምነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል። አዲስ ማለዳም ኢ-መደበኛ በሆነና ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር ባደረገቻቸው አጫጭር ቆይታዎች እነዚህን እይታዎችና አስተሳሰቦች ሰምታለች።

ይሁን እንጂ የተወከሉት መርማሪዎች ነጻና ገለልተኛ አካላት አይደሉም፤ የአሜሪካና የሕወሓትን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው መግባት የለባቸውም። በዚህ ረቂቅም አሜሪካውያን ራሳቸው መርማሪ ራሳቸው ፈራጅ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ እንደፈለጉት መሆን የለባቸውም በማለት በርካቶች ዐዋጁ እንዳይጸድቅ ተቃውሞ አሰምተዋል።

ማዕቀብ ኹሌም ሕዝብን እንጂ መሪዎችን አያስርብም፤ በምንም መልኩ ሊጸድቅ አይገባም። በረቂቁ አንቀጽ 10 ላይም በወንጀል የተሳተፉ የታጠቁ ተዋናዮች የሚለው አገላለጽ፣ ሚሊሻዎችን እና እንደ ፋኖ ያሉ አደረጃጀቶችን ለማዳከም የታቀደ ነው በሚል ሥጋታቸውን የሚያስቀምጡም አሉ።

ረቂቁን መጀመሪያ ማን ሊያስበውና ሊያዘጋጀው ይችላል?
ረቂቁ በማን ታስቦ በማን እንደተዘጋጀ አሁንም ግልጽ አይደለም። በሕወሓት ተዘጋጅቶ ለአሜሪካ ሴናተሮች እንደተላከ የሚጠቁሙ ቢኖሩም፣ አንቀጽ 10 ላይ በሰብዓዊ መብቶችና በዜጎች ግድያ ላይ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል ተብለው ከሰፈሩ አካላት መካከል አንዱ ሕወሓት ነው።
ሆኖም ሕወሓት ቢያዘጋጀው ኖሮ እንዴት ሥሙ በወንጀል ይጠቀሳል የሚሉ ቢኖሩም፣ ሕወሓት አላዘጋጀውም፤ እንዲያውም አሁን እየደገፈው ያለው እሱ የደገፈውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሚቃወመው፣ በዚህ መንገድ ውድቅ ይደረጋል እኔም ከተጠያቂነት እድናለሁ የሚል ስሌት ይዞ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።

የሕግ ባለሙያውና ጠበቃው አንዷለም የሚያምኑት ግን የረቂቁ ሐሳብና ይዘት በሕወሓት እንደተዘጋጀ ነው። እርሳቸውም አራቱም የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በአንድ ቀን የመጣላቸው ሐሳብ ወይም አንድ አሜሪካዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሰበኝ ብሎ ድንገት የመጣለት ሐሳብ አይደለም። ረቂቁን አዘጋጅቶ የላከው ሕወሓት/ጌታቸው ረዳ ሊሆን ይችላል። ሕወሓት ከኢትዮጵያ በዘረፈው ተዝቆ በማያልቅ ሀብቱ ተጠቅሞ እንዲጸድቅለት ሠርቶ የላከው ራሱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ዐዋጆች በሕወሓት ላይ እንዲጣሉ ተሠርቶ እንደነበር አንስተውም፣ በወቅቱ ሐሳቡን ያመነጩት አሜሪካውያን ሳይሆኑ በውጭና በአገር ውስጥ የነበሩ የሕወሓት ተቃዋሚ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ አውስተዋል። አሁን ደግሞ ሕወሓት ተቃዋሚ ሆኖ ሲመጣ ይህን ሐሳብ ሊጠቀምበት እንዳሰበ ነው የሚያምኑት።

በዚህም ሕወሓት ረቂቁ እንዲጸድቅ እየደገፈ ያለው ኢትዮጵያውያን ተቃውመው ውድቅ እንዲያደርጉት ነው የሚሉ ወገኖችን ሐሳብ ባለሙያው በማጣጣል፣ ሕወሓት ረብጣ ገንዘብ ከፍሎ ያዘጋጀው በመሆኑ መደገፉ የሚደንቅ አይደለም የሚል ሐሳብ አላቸው።
‹‹ወትሮም ቢሆን በፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን 13 ጊዜ ጉዳይ አድርገው ሲሰበሰቡ ዓላማቸው ሕወሓትን መታደግ ነበር። የትግራይ ኃይሎች አማራ ክልል ገብተው የሚሠሩት ግፍ አንድም ቀን አሳስቧቸው አያውቅም። በወቅቱ የነበራቸው አቋምም ይታወሳል። አሁንም የዚህ ረቂቅ ዓላማ ተኩስ እንዲቆም በማድረግ ሕወሓትን ተደራዳሪ አካል አድርጎ የፌዴራል ሥልጣን ተካፋይ እንዲሆን ማድረግ ነው።›› ብለዋል።

በአንጻሩ የረቂቁን መጽደቅ የሚደግፉ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሕወሓት ሊያዘጋጀው ይችላል የሚል ጥርጣሬ የላቸውም። የአሜሪካ ሴናተሮች በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን ግፍ በመመልከት ያዘጋጁት ረቂቅ ነው ብለው ያምናሉ።

ኤስ 3199 (S 3199)
በአሜሪካ ሕግ ሲወጣ የሚመለከታቸው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ኮንግረስ) የሚባሉ ኹለት ተቋማት አሉ። ስለሆነም በተወካዮች ምክር ቤት የወጣ ሕግ ከጸደቀ በኋላ በሴኔት በኩልም ማለፍ ስላለበት ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ይላካል። ሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱም በደረሰው ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ ወደ ፕሬዝዳንቱ ይልካል።

በኹለቱ ምክር ቤቶች ጸድቆ የተላከውን ፕሬዝዳንቱ ከፈረመበት በኋላም በሦስቱ አካላት ጥምረት ሕግ ሆኖ ይወጣል። የሕግ ባለሙያው አንዷለም እንደገለጹትም፣ ‹‹ኤስ 3199›› የ‹‹ኤች አር 6600›› ቅጅ (copy) ነው።

የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ከቀናት በፊት ‹‹ኤች አር 6600›› ማዕቀብ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራትን የፀጥታ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት በሌሎች ኃይሎች በጎ ፈቃድ እንዲንጠለጠል እና ራሷን የማትከላከል ሽባ አገር የሚያደርጋት እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ማዕቀቡ በኢትዮጵያ ላይ የሚጸድቅ ከሆነ የዐስር ዓመት ቆይታ እንዳለው ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here