በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን የመድኃኒት ዕጥረት ተከስቷል ተባለ

0
1287

በጦርነቱ በጤና ተቋማቱ ላይ ብቻ በአንድ ወረዳ 22 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን ዝቋላ ወረዳ ሥር በሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የመድኃኒት ዕጥረት መከሠቱን ከወረዳው የጤና ቢሮ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
በዝቋላ ወረዳ ሥር የሚገኙ የሕክምና ተቋማት የተለያዩ መድኃኒቶች ዕጥረት እንደገጠማቸውም የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ እስጢፋኖስ ወንዳዬ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኃላፊው እንደሚሉት ከሆነ፣ የዝቋላ ወረዳ ከነሐሴ 19/2013 ጀምሮ እስከ ኅዳር ወር ማገባደጃ 2014 ድረስ በጸጥታ ችግር ውስጥ ቆይቶ አሁን ላይ አንፃራዊ ሠላም በመምጠቱ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች መደበኛ ሥራቸውን ቢጀምሩም፣ የመድኃኒት ዕጥረት እንደገጠማቸው ነው ማወቅ የተቻለው።

የተለያዩ የመድኃኒት ዕጥረቶች አሉ የሚሉት እስጢፋኖስ፣ ዕጥረቱ በዋነኝነት የተከሠተው በሦስት የመድኃኒት ዓይነቶች መሆኑን ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት። ማግኘት ካልቻሏቸው የመድኃኒት ዓይነቶች መካከልም ለአዋቂዎች የሚሆን ‹ሜትሮንዳይዞል› የተሠኘው መድኃኒት አንዱ ሲሆን፣ ኃላፊው “የሜትሮንዳዞል መድኃኒት ሙሉ ለሙሉ የለም” ሲሉ አሳውቀዋል።

ኃላፊው መድኃኒቱን በሌላ ቦታ ቢፈልጉም ማግኘት እንዳልቻሉ ያመላከቱ ሲሆን፣ ለአብነትም ጎንደር ሔደው ባዶ እጃቸውን መመለሳቸውን ነው ያብራሩት።

ከእስጢፋኖስ ገለጻ መረዳት እንደተቻለው ከሆነ፣ ከሜትሮንዳይዞል በተጨማሪ ከ‹አንቲባዮቲክስ› መድኃኒቶች መካካል ‹ዶክቲሳይክሊን› የተሠኘው የመድኃኒት ዓይነት እና ሕፃናትን ከተቅማጥ በሽታ ለመፈወስ የሚያስችሉ የመድኃኒት ዓይነቶች ዕጥረት ማጋጠማቸው ነው።
ሕወሓት በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት መሠንዘሩን ባለማቆሙ ተፈናቃዮች በመበራከታቸው፣ ከጎንደር ያመጡት ወደ 410 ሺሕ የሚሆን የበጀት መድኃኒት ለኹሉም ማኅበረሠብ ሊያዳርስ አልቻለም ሲሉ ነው ዕጥረቱን እስጢፋኖስ የገለጹት።
በሌላ በኩል፣ የዝቋላ ወረዳ በጦርነቱ ምክንያት በጤና ተቋማት ብቻ ወደ 22 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትና መድኃኒት በሕወሓት ታጣቂዎች እንደወደመበት ነው ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

በዝቋላ ወረዳ አምስት የጤና ጣቢያዎች እንደነበሩ የገለጹት እስጢፋኖስ፣ ከአምስቱ ጤና ጣቢያዎች መካከል አራቱ ማለትም ፅፅቃ፣ ሚሽራ፣ አርሽዋ እንዲሁም ቀዳሚት የሚባሉት የጤና ተቋማት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ሕወሐት መጠነ ሠፊ ውድመት እንዳደረሰባቸው አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ የዝቋላ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች መዘረፋቸውንም ነው ኃላፊው በዝርዝር ያብራሩት።

በመሆኑም፣ አሁን ላይ ለገጠማቸው የመድኃኒት ዕጥረት ዋነኛ ምክንያቱ በጦርነቱ የደረሰው ውድመት ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት የገጠመው መፈናቀልም በሥራ መዋቅራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደሩ ግዥ ማከናወን አለመቻሉ ለዕጥረቱ ተጨማሪ ምክንያት ኾኗል ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዋግኽምራ ዞን ጤና ቢሮ ኃላፊ ኪዳት አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እስካሁን የመድኃኒት ዕጥረት አለ ሲባል እንዳልሰሙና ያልተወሰደ መድኃኒትም እንዳለ ነው የጠቆሙት።
ዕጥረት ገጥሟል ተብለው የተጠቀሱትን የመድኃኒት ዓይነቶች በተመለከተም ከገበያም የሚጠፉበት አጋጣሚ ስላለ ተተኪ መጠቀም እንደሚያስፈግ ነው ምላሽ የሠጡት።

አዲስ ማለዳ ከኹለት ሳምንት በፊት ባስነበበቸው ዕትሟ፣ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ጦርነቱ አለመቋጨቱን ተከትሎ በሕወሓት ጥቃት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ከ30 ሺሕ በላይ ሠዎች የመጠለያ ዕጥረት እንደገጠማቸው መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here