የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ተከስቶ ኹሉንም አገራት ለማዳረስ ጊዜ አልፈጀበትም ነበር። በኹለት ዓመት ቆይታው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አጥቅቶ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ እስካሁን ዘልቋል። ወረርሽኙ ይፋ ሲደረግ ገዳይነቱ በጣም አሳሳቢ እንደነበር ይታወሳል። እያደር ግን ለወረርሽኙ የነበረው ፍራቻ እየቀነሰ መጥቷል። ዓይነቱን እየቀያየረ አንዳንድ ጊዜ ይበልጥ ተስፋፊ እየሆነ በብዛትም እየገደለ ቢመጣም፣ አስፈሪነቱ ግን እያደር መቀነሱን ለማወቅ ተግባራዊ የሚደረጉትን ክልከላዎች ማነፃፀሩ በቂ ነው። ዴልታ የሚባለው ከባዱ ዝርያ ሲከሠት እንኳን፣ አገራትም ሆኑ ግለሰቦች የመጀመሪያውን ያህል መሥጋትም ሆነ መጠንቀቅ አልታየባቸውም ነበር።
ወረርሽኙ በማዕበል መልክ ደግሞ ደጋግሞ እየተከሠተ መላው ዓለምን በስፋት ሲያዳርስ የጎጂነት መጠኑም እንደዛው ሲለያይ ቆይቷል። በቅርቡ የተከሰተውና ኦሚክሮን የተሰኘው ዝርያ ይፋ ከሆነ ወዲህ ከፍጥነቱ አኳያ በሥርጭት አድማሱ ተወዳዳሪ እንደሌለው ተነግሯል። ይህ ቢሆንም ግን ገዳይነቱና አሰቃይነቱ ከሌሎቹ የተሻለ በመሆኑ መዘናጋቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩ ይነገራል።
ቫይረሱ ያን ያህል ጎጂ አይደለም በሚል ከተከሰተው መዘናጋት ጎን ለጎን፣ ሥርጭቱ ወደማብቃቱ ስለሄደ ነው አደገኛነቱ የቀነሰው በሚል የሚሠነዘር መላምት ምንም ዓይነት ማስረጃ የሌለው ምኞት እንደሆነ ተነግሯል። የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ወረርሽኙ ባህሪውን እየቀያየረ ከሰው ልጆች ጋር ለብዙ ዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል ነው።
ከወረርሽኙ ጋር በተገናኘ የሚወጡ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የሥርጭቱ ከፍተኛው መጠን እንዳለፈ የሚያሳዩ ይመስላል። በርካቶች በብዛት የተያዙበት ጊዜ አልፎ የሚያዙትም ሆነ የሚሞቱት ቁጥር መቀነሱ የወረርሽኙ ነገር እያበቃለት ነው በሚል ግምታቸውን የሚሰጡ አሉ። ይህ ግን የተሳሳተ እንደሆነ ዓለም አቀፉ ተቋም ማስታወቁን ‹ሜዲካል ዴይሊ› ዘግቧል።
በሌላ በኩል፣ የዝርያው ዓይነት ከቀደሙት የቫይረስ ዓይነቶች ሲነፃፀር ጎጂነቱ አነስተኛ መሆኑም የማብቂያው መጀመሪያ ነው በሚል የሚያዘናጉ መረጃዎችን የሚያወጡም ግምታቸውን በማስረጃ ማስደገፍ ስለማይችሉ የነበረው ጥንቃቄ ባለበት እንዲቀጥል ተመክሯል። ሕብረተሰቡ ሌላ ዓይነት የከፋም ሆነ በመጠኑ ጎጂ የሆነ ዝርያ ሊከሰት እንደሚችል ገምቶ ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት ተብሏል።
ወቅቱ ቫይረሱ ሊጠፋ ነው የሚባልበት ሳይሆን ሌሎች አዳዲስ ዝርያዎች ሊከሠቱ የሚችሉበት ጊዜ ነው ብሎ መጠንቀቁ የተሻለ እንደሚሆን ተነግሯል። አዲስ ዓይነት ዝርያ እንዲከሠት ኹኔታዎች ምቹ ናቸው ያለው ተቋሙ፣ ኦሚክሮን የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብ አደገኛ እንደሆነ አሳውቋል። ቢያንስ ለቀጣይ ኹለትና ሦስት ዓመታት ከሠዎች ጋር አብሮ ሊኖር ስለሚችል ተባብሮ ሥጋትን ለመቀነስና ችግሩን ለመቋቋም መሞከር ይገባል ተብሏል። ወረርሽኙን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በእንዝህላልነት ከማጓተት ይልቅ በርብርብ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ በጋራ መሠራት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል።
እስካሁን ከ350 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃውና 6 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ለሞት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ አሁንም መስፋፋቱንም ሆነ መግደሉን አላቋረጠም። ኦሚክሮን ከተከሠተ ወዲህ ፍጥነቱም ሆነ ክትባትን የመቋቋም ብቃቱ ከፍተኛ ቢሆንም፣ “ገዳይና ያንያህል ጎጂ አይደለም” በሚል የተፈጠረው መዘናጋት መዘዝ ያመጣል ተብሏል። ለወደፊት ሌላ ከባድ ዝርያ የሚከሠት ከሆነ ሕብረተሰቡ በአጠቃላይ በሽታው አደገኛ አይደለም የሚል ግምት እንዲኖረው ስለሚያደርግ፣ ለወደፊቱ አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።
ኮሮና ቫይረሱ ተዳክሟል የሚለው ግምት ብዙዎችን ሊያሳስትና ለሚኖረው የጥንቃቄ ጉድለት በር የሚከፍት እንደሆነም እየተነገረ ነው። ኦሚክሮን ዝርያ የቀደሙትን ያህል ጎጂ ነው ባይባልም፣ የጤና ተቋማት ከነበረባቸው ችግር ላይ ተጨማሪ ችግር ስለደራረበባቸው ሌላ ዝርያ የሚከሠት ከሆነ የተቋማቱን የአገልግሎት ብቃት እጅጉን ያዳክመዋል ተብሎም ተሰግቷል።
ወረርሽኙ መቼ በቁጥጥር ሥር ይውላል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል የተጠቆመ ሲሆን፣ ለመገመት እንኳን ሳይንቲስቶች ስለተቸገሩ በጣም የተለያየ ጊዜን በመላምታቸው ያስቀምጣሉ ተብሏል። ይህ ስለሆነም መቼ ያበቃል የሚለው ያን ያህል አሳሳቢ መሆን ስለማይኖርበት፣ አሁን ምን ብናደርግ ሥርጭቱን መቀነስና ወረርሽኙን ማስቆም ይቻላል በሚለው ላይ መሥራት ይሻላል ሲል ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ስለጥንቃቄ አስፈላጊነት አተኩሮ ተናግሯል።
የኦሚክሮን ገዳይነት መጠን
አዲሱ ኦሚክሮን የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የገዳይነቱ መጠን 0.16 በመቶ ነው መባሉን ‹ኬ ቢ ኤስ ወርልድ› አስነብቧል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የመሞት ዕድላቸው በዴልታው ዝርያ ከተያዙት በአምስት እጅ ያንሳል የተባለ ሲሆን፣ በዴልታ ከተያዙት መካከል 0.8 በመቶዎቹ ነበሩ የሚሞቱት ተብሏል።
በአሜሪካ በ10 ሺሕ ገደማ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት ውጤቱ ተገኝቷል የተባለ ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካና ካናዳ ከተደረገ ጥናት የአኃዝ ልዩነት አለው ተብሏል። በኹለቱ አገራት የተደረጉ ጥናቶች እንዳሳዩት፣ ኦሚክሮን ከዴልታ ጋር ሲነፃፀር ገዳይነቱ የሚያንሰው በ4 እጥፍ እንደሆነ ነው።
አዲሱ ዝርያ የገዳይነት መጠኑ አነስተኛ ነው ቢባልም፣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመትና የሚስፋፋ እንደመሆኑ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ ግን ከቀደሙት በበለጠ ሰው ሊሞት እንደሚችል ተጠቁሟል። በዴልታ ከተያዙት ቁጥር ከአምስት ዕጥፍ በላይ ሰዎች ከተያዙ የሟች መጠኑ በዛው ልክ ከፍ ስለሚል ብዙ ገዳይ ሊሆን ይችላል ተብሏል። በተለይ የታማሚው ቁጥር ከፍ ካለና ሆስፒታል ፈላጊው በዛኑ መጠን ካሻቀበ አስጊነቱም በዛው ልክ ይጨምራል ተብሏል። በመቶኛ ሲሰላ የኦሚክሮን ገዳይነት ያንሳል የተባለ ሲሆን፣ ከተለመደው ጉንፋን በላይና ከዴልታ በታች ነው ማለት እንደሚቻል ተነግሯል።
አዲስ የኮሮና መመርመሪያ
የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ ሰዎች በሽታው እንዳለባቸውም ሆነ ነጻ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጠው መሣሪያ ጥቂት እንደነበር ይታወሳል። ከናካቴው መመርመሪያው መሣሪያ የሌላቸው ድሃ አገራት ስለነበሩ፣ ናሙናዎቻቸውን ወደሌሎች አገራት እየላኩ ማስመርመርና ውጤቱን ለቀናት መጠበቅ ግድ ይላቸው ነበር። ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ናሙናዎችን ደቡብ አፍሪካ እያስላኩ ያስመረምራሉ የሚባልበት ጊዜ አጥሮ፣ መመርመሪያው ቀስ በቀስ እየተሠራጨ በየአገራቱ ገብቷል። እንደአገራቱ አቅምና ሥልጣኔ ሥርጭቱ ቢለያይም ቀናት ይወስድ የነበረው ሒደት በደቂቃዎች ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል መመርመሪያ ይፋ ኾኗል።
በበለጸጉት አገራት ግለሰቦች በየቤታቸው መመርመሪያው እንዲኖራቸው በማድረግ የጤና ባለሙያዎችን ጫናም ሆነ የመንግሥታቸውን ወጪ ሲጋሩ ይስተዋላል። እንደኛ አገር አቅሙ የሌላቸው ደግሞ ባላቸው አቅም ያገኙትንም ሆነ የተቸሩትን ቆጥበው በነፃ ለሕዝባቸው ግልጋሎት ሲሰጡበት ይታያል። በመንግሥት ተቋማት በነፃ የሚሰጠውን ምርመራ የግሎች ውድ እንደሚያስከፍሉበት ቢታወቅም፣ የቻለና የፈለገ ከፍሎ ቢመረመር ችግር አልነበረውም። ነገር ግን ተመርምሮ ቫይረሱ እንዳለበት የተነገረው ሰው ከሚጠበቀው ቀናት በኋላ ሄዶ በድጋሚ ተመርምሮ ቫይረሱ እንደሌለበት ማረጋገጥ እንደማይችል በጤና ተቋማቱ ሲነገር ተደምጧል።
የመመርመሪያ ዕጥረት ስላለ 10 ቀን የሞላው ተመርምሮ እንደሌለበት ማረጋገጥ አይችልም ቢባልም፣ ሕብረተሰቡ አስቀድሞ ስለመመርመሩ እየዋሸም ሆነ ሌላ ጤና ጣቢያ እየሄደ ከመመርመር አላገደውም። ያም ሆነ ይህ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ምርመራዎች ውጤታቸው በ15 ደቂቃ ውስጥ የሚታወቅ ቢሆንም በአንዳንድ የግል ተቋማት ግን ይህ ሲሆን እንደማይስተዋል የተመረመሩ ይናገራሉ። ይህ ዓይነት ልዩነት እንዲመጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የመመርመሪያው ውድነትና ዕጥረት እንደሆነም ይሠማል።
ከሠሞኑ ግን ፈጣን በቀላሉ ሊሰራጭ የሚችል አስተማማኝ መመርመሪያ መሣሪያ መፈብረኩን ‹ሔልዝ ዩሮፓ› ይፋ አድርጓል። በጀርመን ተመራማሪዎች የተሠራው ይህ መሣሪያ ፈጣን ማወቂያ ነው ተብሎለታል። በዓለም ዙሪያ ከሚመረቱ መሣሪያዎች አንድ አምስተኛ የሚሆኑት የሚሳሳቱና አስተማማኝ ያልሆኑ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ ይህኛው ግን የተለየ ዘዴን ተጠቅሞ የሚያሳውቅ ነው ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። የተለመደው መመርመሪያ ቫይረሱ መኖሩን የሚፈትሽ ሲሆን፣ አዲሱ መሣሪያ ግን ቫይረሱ ያለበት ሰው ላይ የሚመጣውን የበሽታ መከላከል አቅም ለውጥ በማስተዋል የሚያሳውቅ መሆኑ ተጠቁሟል።
ተመሳሳይ ጽሁፎች
የኮቪድ 19 ስጋት እና ያየለው መዘናጋት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
የኮሮና ጫና በርዕዩተ ዓለሞች እና እውነታዎች ላይ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014